የሽሬ ልማት ማህበር ያስገነባው ዲጅታል ቤተመጽሀፍ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ሽረ (ኢዜአ) ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም .የሽረ ልማት ማህበር በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ በ20 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ ያቋቋመው ዲጂታል ቤተመፅሐፍት አገልግሎት መስጠት ጀመረ ። በትግራይ ክልል የሽረ ልማት ማህበር ከሃያ ሰባት ነጥብ ሁለት ሚልዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ያስገነባው ዲጂታል ላብረሪ ለአገልግሎት በቃ። የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረኪዳን በርሔ እንደገለፁት ዲጂታል ቤተ መፅሐፍቱ 248 ኮምፒዩተሮችና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች የተሟላለት ነው ። ዲጂታል ቤመፅሐፍቱ በአንድ ጊዜ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ጨምሮ በሁሉም የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ200 በላይ ተማሪዎችና አንባቢዎች እንዲጠቀሙበት ተደርጎ የተደራጀ ነው ብለዋል ። የዲጂታል ቤተመፅሐፍቱ አስተባባሪ  ወጣት ሓየሎም ዕቋር እንደገለፀው ቤተ መፅሐፍቱ ባለ 50 ሜጋ ባይት የዋይ ፋይ አገልግሎት ያለው ሲሆን ቤተ መዘክርም ጭምር ያካተተ ነው ። ቤተ መዘክሩ የሽሬና አካባቢው የተለያዩ ባህላዊና ጥንታዊ ቅርሳቅርሶች ተሰባስበው ለህዝብ እይታ የሚቀርቡበት ሙዚየም ሆኖ ያገለግላል ብሏል፡፡ ዶክተር ሀብተማርያም አስፋ የተባሉ በጎ አድራጊ ግለሰብ ቤተመዘክሩ ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ባላቸው የተለያዩ ባህላዊና ጥንታዊ ቅርሳቅርሶች እንዲሟላ ያደረጉ ሲሆን በጥሬ ገንዘብም የአንድ ሚሊዮን ብር እገዛ ማድረጋቸውን አስተባባሪው ተናግሯል ። ባለፈው ሰኞ አገልግሎት መስጠት በጀመረው ደጂታል ቤተመፅሐፍት  መጠቀም  ከጀመሩት መካከል ተማሪ ዳዊት ተክለሃይማኖት በሰጠው አስተያየት ዲጂታል ላይብረሪው የተለያየ ጠቀሜታ ባላቸው ሶፍት ኮፒዎች የተሞላ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብሏል። “የኢንተርኔት አገልግሎቱ ፈጣን በመሆኑ በቀላሉ የፈለከውን መፅሓፍ ለማውረድ  የሚያስችል ዲጂታል ላብረሪ ነው” ያለው ደግሞ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሽረ ካምፓስ ተማሪ ገብረህይወት ተወልደብርሃን ነው። በተመፅሐፍቱን ባለፉት አራት ዓመታት በማስገንባት ለአገልግሎት ያበቃው የሽሬ እንዳስላሴ ልማት ማህበር በ1995 ዓም የተቋቋመና በሀገር ውስጥና በውጪ 25 ሺህ አባላት ያሉት ነው ተብሏል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም