ቀጥታ፡

ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ውጤታማ ለመሆን መዘጋጀቱን ገለጸ

ሶዶ ጥቅምት 25 ቀን 2012 የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተዘጋጅቼያለሁ አለ። ክለቡ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ሆኖ ለማጠናቀቅም አቅዷል። የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሆሲሶ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ክለቡ በ2012 የውድድር ዘመን ውጤታማ ለመሆን ይተጋል። ክለቡ በሰው ኃይል አደረጃጀት፣ውጤታማ የስልጠና ሂደትና በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ መስራቱን ገልጸዋል። በክለቡ በክረምት ሰባት ተጫዋቾች ማዛወራቸውን፣አምስት ተጫዋቾች ከታዳጊ ፕሮጀክት ማሳደጉንና ውላቸውን ያጠናቀቁ ተጫዋቾች ውል ታድሷል ብለዋል። የክለቡን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ የሚተገብር የአሰልጣኞች ቡድን ማደራጀቱንም ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል። ክለቡ በውድድር ዘመኑ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁን  አስረድተዋል። የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አቶ ገብረ ክርስቶስ ቢራራ የአካባቢውን የአየር ንብረት ታሳቢ ያደረገ የተግባር ስልጠና፥ጠንካራ የማሸነፍ ሥነ-ልቡናና የቡድን መንፈስ መገንባትን ያካተተ ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ የአካባቢው፣የደጋፊዎችና የክለቡን ፍላጎት የሚያሟላ ተፎካካሪ ቡድን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የክለቡን አቋም ለመፈተሽ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ መደረጉን አስታውቀዋል ። በተያዘው የውድድር ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተዘጋጁ መሆናቸውን የተናገረው የክለቡ አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ ነው ። የአሰልጣኙ የአሰለጣጠን መንገዶች ትጋትና መነቃቃት እንደፈጠረላቸውም ገልጿል። ክለቡ ባለፈው የወድድር ዘመን  ሰባተኛ ደረጃ ይዞ ሊጉን ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ኅዳር 13 ቀን 2012 እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መግለጹ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም