ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል የጸሎት ቀን አወጁ - ኢዜአ አማርኛ
ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል የጸሎት ቀን አወጁ
ጥቅምት 25 ቀን 2012 የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል ለመላው ካቶሊካውያን የጸሎት ቀን አወጁ ፡፡ ጥቅምት 27 ቀን 2012 ዓ.ም የመድኃኔዓለም ዓመታዊ ክብረ በዓል ሲከበር በዕለቱ ሁሉም የቤተክርስቲያኗ ቁምስናዎችና ጸሎት ቤቶች ስለኢትዮጵያ ሰላም፣ ስለሞቱ፣ ስለተጎዱ፣ ስለተፈናቀሉ ወገኖች በጋራ በመሆን ለመጸለይ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ የጸሎት ቀን አውጀዋል። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በኢትዮጵያ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ሞት፣ አካል ጉዳት፣ ሰቆቃና መፈናቀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ በሁሉም ውስጥ ድንጋጤ ፈጥሯል። ''ይህ ሁኔታ ስር የሰደደ መሆኑ ደግሞ የበለጠ እንድንጸልይ፣ የበለጠ ለሰላምና ለእርቅ ስራ እንድንተጋ ሃላፊነት እንድንወስድ ያስገድደናል'' ሲል መግለጫው አመልክቷል። በመሆኑም በኢትዮጵያና በውጭ አገር የሚኖሩ ካቶሊካውያን ምዕመናን የህዝቡን ሰቆቃና መከራ ሰላም ማጣት መድኃኔዓለም ክርስቶስ ተመልክቶ ሰላም እንዲያወርድና እርቅን እንዲያሰፍን ምዕመኑ እንዲማጸን ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ በትህትና መጠየቃቸውን ገልጿል።