ኢትዮጵያ ከጥጥ ልማቱ እንድትጠቀም ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች ይጠበቅባታል

61
ጥቅምት 25 ቀን 2012 አገሪቷ ከጥጥ ልማት የምታገኘውን ጥቅም በማሳደግ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን በቅድሚያ ለስራው ትኩረት መስጠት እንደሚገባት የዘርፉ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች አሳስበዋል። ዓለም አቀፍ የጥጥ ቀንን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከዘርፉ ተመራማሪዎች ጋር አገራዊና የዓለም ተሞክሮዎችን አንስቶ መክሯል። መድረኩ አገሪቷ በዘርፉ ያላትን የማልማት ዓቅሟን ለማሳደግ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች የተሰተፉበት ውይይት ሲሆን ከዚሁ የሚገኘውን ምክረ-ሀሳብም ኢንስቲትዩቱ ለልማቱ ተግዳሮቶች መፍትሔ ለመስጠት ይጠቀምበታል። የጥጥ ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተሩ አቶ ሳምሶን አሰፋ በዚሁ ጊዜ በዘርፉ አሉ ያሏቸውን ተግዳሮቶች ሲያብራሩ፤ በጥጥ ልማት የሚታወቁ አካባቢዎችን አምራቾች ወደ ሌላ ማምረት መመለሳቸውና ምርቱ በባህሪው በተባይ ተጠቂ መሆኑ ይገኝበታል። የተፈጥሮና መልክዓ ምድራዊ ችግሮችን ጨምሮ እንደ ጸጥታ እጦት፣ የተራንስፖርት ችግር፣ እንዲሁም የባለድርሻ አከላት ቅንጅት ችግሮችም አቶ ሳምሶን እንደምክንያት አንስተዋል። ስለሆነም እንደዚህ መሰል መድረኮች ለዘርፉ ተግዳሮቶች መፍትሄን ከማመላከት ጀምሮ የአለምን ተሞክሮና ልምድ በመገንዘብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችለናል ነው የሚሉት። በአለም ከሚመረተው ጠቅላላ ፀረ ተባይ ውስጥ 25 በመቶ የሚጠቀመው የጥጥ ልማት መሆኑ አምራቾቹ ፊታቸውን ወደ ሌሎች ሰብሎች መመለሳቸውን የተናገሩት ደግሞ የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዳዊት ተስፋዬ ናቸው። ዘርፉ ራሱን የቻለ የምርምር ተቋም የሌለው በመሆኑም የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ያመላክታል ያሉት ዶክተር ዳዊት፤ ይህም በመሆኑ አምራቹ ወደ ሰሊጥ፣ ሸንኮራና ሙዝ መመለሱን ይናገራሉ። ከአጠቃላይ የጥጥ ምርቶቻችን ውስጥ 70 በመቶ በሰፋፊ እርሻዎች ቀሪው ደግሞ በአነስተኛ አምራቾች እንደሚመረት የተገለጸ ሲሆን በዚህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ በ13ኛ ደረጃ ያስቀምጣታል። 75 በመቶ የዓለምን የጥጥ ከሚያመርቱ 13 ሃገራት በቀዳሚነት የሚቀመጡት ህንድ፣ ቻይና፣ አሜሪካ ሲሆኑ ወደ ውጭ በመላክ ደግሞ አሜሪካ፣ ህንድና፣ ብራዚል በግንባር ቀድምትነት ተጠቃሾች ናቸው። ቻይና ባላት ከፍተኛ የጥጥ ምርት ክምችት በዓለም የጥጥ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደሆነች ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም