ቀጥታ፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል የበለጸገ የህግ ስርዓት የለም

ጥቅምት 25/2012  በአገር አቀፍ ደረጃ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል የበለጸገ የህግ ስርዓት አለመኖሩን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያካሄደው ጥናት አመለከተ። ኤጀንሲው ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት 88 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆኑ የመንግስት ተቋማት የሳይበር ደህንነት የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ የላቸውም። የሳይበር ደህንነት ሳምንት "ትኩረት ለሳይበር ደህንነት" በሚል መሪ ሐሳብ ትናንት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ የመክፈቻ መርሐ ግብር ተካሂዷል። በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የሳይበር ኢንጂነሪንግ ዲቪዥን ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ የሳይበር ደህንነት ነባራዊ ሁኔታ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ገለጻ በአገር አቀፍ ደረጃ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል የበለጸገ የህግ ስርዓት የለም። ኤጀንሲው በመንግስት ተቋማት ላይ ባካሄደው ጥናት ደካማ የሆነ የሳይበር ደህንነት ስርዓት እንዳለ መረጋገጡንም ገልጸዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ ከሚያስፈልገው የበለጸገ የህግ ስርዓት አለመኖር ባሻገርም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት አንዱ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም በተቋማት ኃላፊዎች ዘንድ ለሳይበር ደህንነት ተገቢውን ትኩረት አለመስጠትና እንደ ትርፍ ስራ አድርጎ ማየት እንዳለም ወይዘሮ ትዕግስት ተናግረዋል። በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የሳይበር ገቨርናንስና ማኔጅመንት ዲቪዥን ኃላፊ አቶ ተመስገን ቅጣው በበኩላቸው ዘርፉ በሌሎች አገሮች ካለው የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ አኳያ ብዙ መሰራት ያለባቸው ስራዎች እንዳሉ ገልጸዋል። የሳይበር ደህንነት ውስብስብና ከፍተኛ አቅም የሚጠይቅ ስራ መሆኑን የገለጹት አቶ ተመስገን፤ በዘርፉ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋራ በመተባበር የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ መጠናቀቁን ተናግረዋል። ኤጀንሲው የተጣለበትን ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትም በዘርፉ የሰለጠኑ ሙያተኞችን ለማፍራት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። እንደ አቶ ተመስገን ገለጻ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሳይበር ደህንነት ሙያ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ከኮምፒዩተር ጋር በተያያዘ መስኮች የሰለጠኑ ባለሙያዎች ናቸው። በዓለም ላይ ዋና ዋና ስጋቶች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የሳይበር ጥቃት እንደሆነ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2018 ያወጣው ዓመታዊ የስጋት ሪፖርት ያመለክታል። ለአብነትም በ2018 ብቻ በተከሰቱ የሳይበር ጥቃቶች በዓለም ላይ የ1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሟል። በኢትዮጵያም የሳይበር ጥቃቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በ2011 ዓ.ም ቁልፍ በተባሉ መሰረተ ልማቶችና ተቋማት ላይ 791 የሳይበር ጥቃቶች መሰንዘራቸውን አውስተዋል። በዓለም ለ16ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው የሳይበር ደህንነት ሳምንት ከጥቅምት 24 እስከ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም