የምርት ገበያ ባለስልጣን ዘመናዊ የግብይት ስርዓቱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የምርት ገበያ ባለስልጣን ዘመናዊ የግብይት ስርዓቱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ
ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ዘመናዊ የግብይት ስርዓቱን ለማስፋት ከቀጥታ ግብይት ፈፃሚዎች ጋር በቅርበትና በትብብር እንደሚሰራ ገለጸ። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የቁጥጥር ስራውንና የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ አባል ያልሆኑ ቀጥታ ተገበያዮች ሊሰሩባቸው በሚገባቸው መመሪያዎች ዙሪያ ግንዛቤ ሰጥቷል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ኦሌሮ ኦፒየው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፣ አባል ያልሆኑ ቀጥታ ተገበያዮች ወደ ገበያው እየገቡ ቢሆንም በሚጠበቀው ልክ እየሰሩ አይደለም። የቀጥታ ግብይት ፈጻሚዎች ከሚባሉት መካከል ላኪዎች፣ አነስተኛ አርሶ አደሮችና የምርት አቅራቢዎች ይጠቀሳሉ። የቀጥታ ግብይት ፈጻሚዎች በተለይ የኦዲትና የፋይናንስ ሪፖርቶችን በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ሲያቀርቡ አይስተዋልም። በመሆኑም ዘመናዊ የግብይት ስርዓትን ለማስፋት፣ ለቀጥታ ተገበያዮቹ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግና ዘመናዊ የግብይት ስርአትን በስፋት እውን ለማድረግ ከቀጥታ ተገበያዮች ጋር በቅርበት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ኢንጂነር ኦሌሮ ገልጸዋል። የግብይት ፈጻሚዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቡድን መሪ አቶ አብደና ማሙዬ፤ ቀደም ሲል ቀጥታ ግብይት ፈጻሚዎች ወደ ገበያው በስፋት እንዲገቡ እውቅና ሲሰጥ እንደነበር አንስተዋል። በዚህም ለ201 ቀጥታ ተገበያዮች እውቅና መሰጠቱን አስታውሰዋል። በቀጣይም ምርት ገበያው የቀጥታ ግብይት ፈጻሚዎችና የግብይት ወኪሎቻቸው ወደ ዘመናዊ አሰራር እንዲገቡ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። በግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው ላይ ከተሳተፉት የቀጥታ ግብይት ፈጻሚዎች ስልጠናው አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል።