ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማሳደግ የፋይናንስ እጥረት እንቅፋት ሆኗል

ጥቅምት 25 ቀን2012 ዓም  ኢዜአ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማሳደግ የፋይናንስና የግብዓት ቁሳቁሶች እጥረት አይነተኛ ችግሮች እንደሆኑበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ''የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮች ማሻሻያና አቅም ማሳደጊያ ፕሮጀክቶችን'' በሚመለከት ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል። በአገልግሎቱ የለውጥና የመልካም አስተዳድር ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው እንደገለጹት በአገሪቷ መጠነ ሰፊ የኤሌክትሪክ የአገልግሎት ችግር ይስተዋላል። ችግሩን ለማቃለል በተለይ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችን የማሻሻልና አቅም የማሳደግ ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ሆኖም የፋይናንስና የግብአት ቁሳቁሶች እጥረት መሰረተ ልማቶችን በሚፈለገው መጠን ለማስፋፋት አይነተኛ ችግር መሆኑን አስረድተዋል። የኃይል አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ክፍያ በአግብቡ ያለመስብሰብ፣ የኤሌክትሪክ ክፍያ ከጊዜውና አገልግሎቱ ጋር የተመጣጠነ ያለመሆንም ሌላኛው ችግር ሆኖ ተጠቅሷል። መንግስት ለዘርፉ ቀደም ሲል ያደርገው የነበረው ድጎማ መቅረቱም ችግሩን እንዲባባስ አድርጎታል። እንደ አቶ እሱባለው ገለፃ ተቋሙ በ2011 ዓ.ም ካገኘው 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ውስጥ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብሩን አሁን ላይ ለማሻሻያና የማስፋፊያ መድቦ እየሰራ ይገኛል። በኤሌክትሪክ ሃይል መሰረተ ልማት ላይ በስፋት የሚስተዋለውን የዘረፋ ወንጀል ለመከላከልም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው ብለዋል። በቀጣይ ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርበውን ኃይል ማሳደግ እንዲሁም በቅርቡ የተደረገውን የታሪፍ ማስተካከያ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል። እስካሁን በአገሪቷ ስምንት ከተሞች የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮች ላይ ማሻሻያ ተደርጓል። በቀጣይም በስድስት ከተሞች ተመሳሳይ ስራ ለማከናወን እቅድ መያዙን መረጃዎች ይጠቁማሉ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም