ቀጥታ፡

ለዘላቂ ሠላም የኃይማኖት ተቋማት የሠላም እሴት ግንባታ ላይ ተከታታይ ስራ እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ

ጥቅምት 25/2012 በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እንዲፈጠር የኃይማኖት ተቋማት የሠላም እሴት ግንባታ ላይ ተከታታይነት ያለው ተግባር ሊያከናውኑ እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ። የአዲስ አበባ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 8ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል። በጉባኤው ላይ የተለያዩ ኃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የመንግሥት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን፤ ቤተ እምነቶች ለዘላቂ ሠላም መረጋጋጥ የሚጠበቅባቸው መወጣት እንደሚኖርባቸው በሰፊው ተነስቷል። የኃይማኖት አባቶች በተለይም  የነገ አገር ተረካቢ ወጣቱን በመግራት፣በማስተማርና ኃይማኖታዊ እሴቶችን በማስረጽ የበኩላቸው እንዲወጡም ነው ጥሪ የቀረበው። በጉባኤው ላይ በቅርቡ በአገሪቷ በተቀሰቀሰው ግጭት ህይወታቸውን ላጡና ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉም የጸሎት ሥነ ስርዓት ተካሂዷል። የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በኃይማኖት ተቋማት በኩል የሠላም እሴት በመገንባትና አንድነትን በማጠናከር ረገድ አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ''ይሁን እንጂ አሁን ያለንበት ሁኔታ ከዚህ በላቀ ደረጃ ለሠላማችን በጋራና በትብበር መስራት የሚያስፈልግበት ወሳኝ ጊዜ ነው''፤ በመሆኑም አስተማማኝ ሠላም እንዲኖር በማህበራዊ ግንኙነት ዙሪያ ተቀባይነት ያላቸው እሴቶችን መሰረት ያደረገ የሠላም እሴት ግንባታ መስራት ይጠበቃል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። እንደ ቀሲስ ታጋይ ገለጻ በተለይም ወጣቱ ከስሜታዊነት በመራቅና በማስተዋል መጓዝ ይኖርበታል፤ በእኛ በኩልም ወጣቱ የመከባበር፣ የመደማመጥ፣ የአብሮነት እሴት እንዲያደብር የቤት ስራችንን መስራት ይኖርብናል ብለዋል። በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ኃይማኖትን፣ ብሄርንና ግላዊ አስተሳቦችን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ ዘመቻዎች የዜጎችን ማህበራዊ መስተጋብር እያላላው መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ጸሐፊው፤ በተለይም ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ጥንቃዌ ሊደረግ እንደሚገባም አመልክተዋል። ''የዘረኝነትና ጠባብ ብሄረተኝነት አመለካከትና ተግባር በኃይማኖቶችም ይሁን በኢትዮጵያዊ ባህላንች ፍጹም ተቀባይነት የላቸውም፤ ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል'' ሲሉም ነው ያሳሰቡት። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና የጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮሃንስ ምትኩ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኃይማኖት ተቋማት በዜጎች መካከል የመከባበርና በሠላም አብሮ የመኖር እሴቶች እንዲገለብቱ በማድረጉ ረገድ የማይዘነጋ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ለአብነት አንስተዋል። ይህ እሴት ለቀጣዩ ትውልድ መሰረት እንዲሆን ኃይማኖቶች ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ያቀረቡት ኃላፊው ''እናንተን ለመከፋፈል ለሚሞክሩ እድል ሳትሰጡ፣ አንድነታችሁን በማጠናከር ለሕዝቦች ሠላም እንዲሁም የትውልድን ሞራልና ስነ-ምግባር ለማጎልበት መስራት ይጠበቃል ብለዋል። የአዲስ አበባ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በበኩላቸው ጉባኤው በዚህ ዓመት የሠላም ባህል ግንባታ ላይ ሰፊ ስራ ለመስራት እቅድ መያዙን ጠቅሰዋል። ለአብነትም በወጣት፣ ሴቶችና የነዋሪዎች ፎረሞች ጋር በመተባበር የምክክር መድረክ እንደሚካሄድ ጠቁመው አለመግባባት ባሉባቸው ቦታዎች ላይ እርቅ እንዲፈጠር ጉባኤው ከባለሙያዎች ጋር በመሆን ትምህርትና ስልጠና እንደሚሰጥም አብራርተዋል። በመድረኩ ለአዲስ አበባ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቀድሞ የቦርድ አባላት፣ ለሰብሳቢዎችና ለኃይማኖት አባቶች እውቅና ተሰጥቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም