የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የጤና መረጃ ልውውጥ አሰራር ሊዘረጋ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የጤና መረጃ ልውውጥ አሰራር ሊዘረጋ ይገባል
አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2012 የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የጤና መረጃ ልውውጥ አሰራር እየተዘረጋ መሆኑ ተገልጿል። ለሁሉም ተደራሽ የሆነ ዓለም አቀፍ የጤና መረጃ ልውውጥ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ለ3 ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ ከአፍሪካና ከተቀሩት ዓለማት እንዲሁም ከአገሪቷ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ነው። የጤና ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር የቆየሰው ወርቁ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት "የጤና መረጃ ልውውጡ የጤና መረጃን ዘመናዊ ማድርግ፣ የታካሚዎችን መረጃ በአንድ ቦታ መዝግቦ መያዝና ለሌሎች ተቋማትም በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል የታሰበ ነው።" የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የሚያግዝና ከግሉ ዘርፍና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ውይይት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። ጉባዓው ህብረተሰቡ ጤናውን እንዲጠብቅና የሚሰጠውን አገልግሎት በአግባቡ ለመስጠት የሚያስችል ነውም ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው አገራትም የልምድ ልውውጥ የሚካሄድበት መሆኑን ተናግረዋል። ከተለያዩ የዓለም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መረጃዎችን በቅንጅት እንዴት በአንድ ቦታ ማግኘት ወደሚያስችል አሰራር መዘርጋት በሚለው ዙሪያም ልምድ እንወስዳለን ብለዋል። መረጃዎችን ማናበብ ወይም አንዱ የሌላውን መረጃ ማግኘት እንዲችል ማድረግም ከአሰራሩ ይጠበቃል ብለዋል። በተለይም ከጤና ተቋማትና ከባለሙያዎች ላይ የታካሚዎች መረጃ በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል ዲጂታላይዝድ የሆነ መረጃ ለመዘርጋት የሚያስችል ነው ብለዋል። ጉባኤው የተለያዩ የጤና መረጃዎችን ወደ አንድ ማምጣትና መረጃዎችን በመጠቀም ለታካሚዎች የሚሰጠውን አገልግሎት ማሻሻልና ባለሙያዎች የሚሰጡት ህክምና ጥራቱን እንዲጠብቅ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መረጃ አጠቃቀም ፓርትነርሺፕ ዳይሬክተር ዶክተር ህብረት አለሙ በበኩላቸው ጉባዔው መረጃን ለውሳኔ በመጠቀምና በማዘመን በኩል በዓለም ያሉትን መልካም ተሞክሮዎች በመውሰድ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥመን ለመጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል። በአገሪቷ በኮምፒዩተር አማካይነት እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል ጉባዔ መሆኑንም በመጠቆ። ተገልጋዩ ጥራት ያለው አገልገሎት እንዲያገኝና መረጃ ጠፍቷል በማለት በተገልጋዮች ላይ የሚደርሰውን መጉላላት የሚቀንስ አሰራር መሆኑንም ተናግረዋል። በአገሪቷ የጤና ተቋማት ያለውን የአይ ሲ ቲ መሰረተ ልማት ለማሻሻልም ከኢትዮ -ቴሌኮም ጋር በመሆን በጋራ እየሰራን ነውም ብለዋል። የኮምፒውተር፣ የሲስተም እና የተለያዩ ጥገናዎችን ለማካሄድ የሚችሉ ባለሙያዎችን በመጠቀምም የተለያዩ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ገልጸው ይህን የበለጠ ለማሳለጥም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህም በበርካታ የመንግስት ሆስፒታሎች ላይ በኢትዮ-ቴሌኮም የኔትወርክ መሰረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። 150 በአይ ሲ ቲ የተመረቁ ወጣቶች በጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ ተጨማሪ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑንም ተናግረዋል። ከ21 አገራት የተውጣጡት ተሳታፊዎች በጉባዓው የተገኙ ሲሆን ተቋሙ እ.አ.አ በ2013 የተመሰረተ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።