ቀጥታ፡

የአፍሪካ የአልባሳትና የፋሽን ዐውደ ትርኢት ሊካሄድ ነው

አዲስ  አበባ  ጥቅምት  25/2012  ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ ለአራት ቀን የሚቆይ የአፍሪካ አልባሳትና የፋሽን ዐውደ ትርኢት ሊካሄድ ነው በዐውደ ትርኢቱ ከ25 አገራት በላይ ከሚሆኑ አገራት ከ280 በላይ ተሳታፊዎች ምርቶቻቸውን ለእይታ የሚያቀርቡም ይሆናል። ከሶስት ሺህ በላይ ሰዎች ዐውደ ትርኢቱን ይጎበኛሉ ተብሎም ይጠበቃል። የዐውደ ትርኢቱ አዘጋጅ አቶ እስክንድር ነጋሲ ዐውደ ትርኢቱ በኢትዮጵያ ሲካሄድ ይህ ለአስራ አንደኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁመው የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ከጨርቃ ጨርቅ ምርቶች በተጨማሪ የቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ምርት ማካተቱ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ ጎሹ ነጋሽ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም አገሪቷ ከ70 በመቶ በላይ የጨርቃ ጨርቅ ምርት ግብአቶችን ከውጭ አገር ታስገባ ስለነበር የምርቱ ዋጋ እንዲወደድ አድርጎ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁንና የእስካሁኖቹ ዐውደ ትርኢቶች በፈጠሩላቸው የገበያ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቅመው በአገሪቷ እንደ ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ያሉ ፋብሪካዎች ምንም አይነት ግብዓት ከውጭ ሃገራት ሳያስገቡ ምርት ማምረት በመጀመራቸው በምርቱ ላይ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር አድርጓል ብለዋል። ዐውደ ትርኢቱ ከዚህ በተሻለ መንገድ የቆዳ ምርቶችን እሴት ጨምሮ በመላክ ከቆዳና የቆዳ ምርት ውጤቶች የሚገኘውን ገቢ የማሳደግ ሚና ይኖረዋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃይለኪሮስ ደባሳይ ናቸው። ዐውደ ትርኢቱ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች የምርቶቻቸውን መዳረሻ ለማስፋት እንደሚረዳቸውም ተገልጿል። ዐውደ ትርኢቱ ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም