ቀጥታ፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ2019 የፌሞዛ አዋርድ አሸናፊ ሆነ

ጥቅምት  25/2012 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዓለም ዓቀፍ ነጻና ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠና ፌዴሬሽን የሚሰጠውን የፌሞዛ ሽልማት የ2019 ዓመት አሸናፊ ሆነ። ፌሞዛ ትርፍን መሰረት አድርጎ ያልተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ሲሆን ከ60 በላይ አገራትን በአባልነት አሰባስቧል። ፌሞዛ በአባል አገራት ውስጥ የሚገኙና ወደ ለውጥ እየመጡ ያሉ አገራትን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማሳደግ የሚሰራ ድርጅት ነው። ተቋሙ አለም አቀፍ ልምዶችን በማካፈል ፣ ባለሙያዎችን በማሰልጠን፣ ቴክኒካዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ በመስጠት፣ ቴክኖሎጂዎችን በማጋራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አዋጪ እንደሆኑም ይደግፋል። ተቋሙ ሽልማቱን የሚሰጠው በስራ ፈጠራ፣ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚን በማሻሻልና በማሳደግ፣ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር፣ በዘርፉ የወጪ ንግድ እንዲያድግ በማስቻል፣ ቀልጣፋ የመሰረተ ልማት ግንባታ በማከናወን፣ የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ ነው። የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ተሸላሚ የሆነው የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በፍጥነት ወደምርት እንዲሸጋገሩ በማድረጉ፣ የስራ ፈጠራና የኤክስፖርት አቅም እንዲጎለብት በማስቻሉ፣ ከከባቢ አየር ጋር ተስማሚ የሆኑና ከብክለት ነጻ የሆኑ ፓርኮችን በመገንባቱ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ኮርፖሬሽኑ በመጪው ሳምንት ማክሰኞ ህዳር 2 ቀን 2012 ዓም በምእራብ አውሮፓ የፈረንሳይ ሪቬራ ግዛት በምትገኘው ሞናኮ ውስጥ በሚካሄደው የዓለም ዓቀፍ ነጻና ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠና ፌዴሬሽን ጉባኤ ላይ በሚሰናዳው ስነ-ስርዓት ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል። ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማልማት ለምርት ዝግጁ ያደረገ ሲሆን በዚህም ከ55 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል እንዲያገኙ እድል ፈጥሯል። በተያዘው በጀት ዓመት አራት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባትና በግንባታና በምርት ሂደት ላይ የሚገኙ ሰባት ፓርኮችን በመደገፍ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም