የአክሱም ወጣቶች ማህበር በ36 ሚልዮን ብር ወጪ ሁለ ገብ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ሊገነባ ነው።

አክሱም ጥቅምት 25/ 2012  የትግራይ ወጣቶች ማህበር የአክሱም ቅርንጫፍ በ36 ሚልዮን ብር ሁለገብ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ለመገንባት መዘጋጀቱን አስታወቀ ። በከተማው በቂ የመዝናኛ ማዕከላት ባለመኖራቸው ወጣቶች ለሱስና ተያያዥ ጉዳዮች ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጸዋል። የአክሱም ከተማ ወጣቶች ማህበር ሊቀ መንበር ወጣት ሓዱሽ ፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለጸው የክልሉ ወጣቶች ማህበር ባካሄደው ጉባኤ በክልሉ በሚገኙ ታላላቅ ከተሞች የወጣቶች መዝናኛ ማእከላት ለመገንባት ተወስኖ ነበር ። ውሳኔውን ተከትሎ ማህበሩ በአክሱም ከተማ ሁለገብ የወጣቶች መዝናኛ ማእከል ለመገንባት የሚያስችለውን አንድ ሺህ ካሬ መሬት ከከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንት መረከቡን አስረድተዋል። ሁለገብ የመዝናኛ ማእከሉ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ግንባታው ለማስጀመርና በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን ወጣት ሓዱሽ ተናግሯል። የሚገነባው ዘመናዊ ሁለገብ መዝናኛ ማእከል ባለ አራት ፎቅ ሲሆን አጠቃላይ ወጪው 36 ሚሊዮን ነው ። የወጪውን 70 በመቶ የክልሉ ወጣቶች ማህበር የሚሸፍነው ሲሆን ቀሪው በከተማው አስተዳደር የሚሸፈን መሆኑን ከወጣት ሓዱሽ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ። የማእከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ ቤተ መጽሐፍት፣ካፊቴሪያ ፣የጂምናስቲክና የተለያዩ መጫወቻዎችን ጨምሮ በርካታ መዝናኛ ስፍራዎች ይኖረዋል ። በከተማዋ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ከሚያዘወትሩ ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ካሕሳይ በየነ በሰጠው አስተያየት ከአሁን በፊት በአልባሌ ቦታዎችን በመዋል ለሱስ ተጋላጭ እንደነበር ተናግሯል። ከሱስ ለመላቀቅ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ቢጀምርም ክፍያው የሚቀመስ አይደለም ብሏል ። ወጣቶች የሚያዝናና እና ስብእናን የሚገነባ ሁለገብ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ባለመኖሩ ወጣቶች በመጠጥ ቤትና ሌሎች አላስፈላጊ በሆኑ ስፍራዎች እንዲውሉ የተገደዱበት ሁኔታ እንደነበር አስረድቷል። ማህበሩ የመዝናኛ ማእከል ለመገንባት መዘጋጀቱ ብዙ ወጣቶች መልካም ስብእና እንዲገነቡ የሚያግዝ በመሆኑ የሚበረታታ ነው ብሎታል ። ከከተማዋ እድገት እና የወጣቶች ብዛት አንጻር ሲታይ ወጣቶች የሚዝናኑበት በቂ ቦታ እንደሌለና አሁን ትኩረት መሰጠቱ ተገቢ ነው ያለው ደግሞ ወጣት አሸናፊ የውኋላ ነው። ከስራ ስአት ውጪ በስፖርታዊ አንቅስቃሴ እና ሌሎች መዝናኛዎች ከጓደኞቼ ጋር ለመዝናናት ብንፈልግም የመዝናኛ ማዕከል ባለመኖሩ ተቸግረን ቆይተናል ብሏል። በባህሉና ታሪክ የሚኮራ እና በስነ ምግባር የታነጸ ወጣት ለማፍራት ወጣቶች እየተዝናኑ እርስበርሳቸው የሚማማሩበትና መረጃ የሚለዋወጡበት ዘመናዊ የመዝናኛ ማዕከል እንደሚያስፈልግ የተናገረው ደግሞ ወጣት ሸዊት ተወልደ ነው።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም