በግራር ጃርሶ ወረዳ በማህበር ተደራጅተው ወደሥራ የገቡ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በግራር ጃርሶ ወረዳ በማህበር ተደራጅተው ወደሥራ የገቡ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ተናገሩ
ፍቼ (ኢዜአ) ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም---በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናገሩ። የዞኑ ኢንተርኘራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ 41ሺህ የሚጠጉ ወጣቶችን በዘንድሮ ዓመት ወደሥራ ለማስገባት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል። በወረዳው ወደ ሥራ ከገቡ ወጣቶች መካከል አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንዳሉት ህብረተሰቡና መንግስት ባደረጉላቸው ድጋፍ በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተው ውጤታማ መሆን ችለዋል። በግብርና፣ በአሸዋና ጠጠር እንዲሁም በቆዳ እና እደ- ጥበብ ሙያ ተሰማርተው ጥሩ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ቋሚ ንብረት ማፍራት እንደቻሉም ነው የገለጹት። ወደ ሥራ ከገቡ ወጣቶች መካከል በወርጡ ቀበሌ "ደራራ" በሚል ስያሜ ከአሥር ወራት በፊት በመአድንና እደ ጥበብ ሥራ ለመሰማራት የተደራጀው ማህበር ሊቀመንበር ወጣት አሰበ ወሌ አንዱ ነው። የማህበሩ አባላት ከወረዳው አስተዳደር በተሰጣቸው 3ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ አሸዋ፣ ጠጠርና ድንጋይ አምርተው በመሸጥ በነፈስ ወከፍ በወር እስከ 1ዐሺህ ብር እያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል። በዚህም ከቤተሰብ ተረጂነት ከመላቀቃቸው በተጨማሪ በማህበራቸው ለአስር ወጣቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ለራሱ መኖሪያ ቤት ለመስራት ከፍቼ ከተማ አስተዳደር ቦታ ተረክቦ የግንባታ ሥራ መጀመሩን የጠቀሰው ወጣት አሰበ፣ ሌሎች ወጣቶች ባገኙት የሥራ አማራጭ እንዲሰማሩም መክሯል። የጌጠኛ ድንጋይና ቅርጻ ቅርጾችን በመስራት ለገበያ የሚያቀርበው የደብረ ሊባኖስ ሽርክና ማህበር ፀሐፊ ወጣት ጫልቱ ጎንፋ በበኩሏ፣ ማህበሩ በተቋቋመ ስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ የአባላቱን ወርሃዊ ገቢ ከ2 ሺህ ብር ወደ 3 ሺህ ብር ማሳደጉን ተናግራለች። "ማህበሩ በቅርቡ ገልባጭ የጭነት ተሽከርካሪና ሌሎች ምርቱን ለማምረት የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ለመግዛት በዝግጅት ላይ ነው" ስትልም ነው የገለጸቸው። ማህበሩ ውጤታማ እንዲሆን የአካባቢው ነዋሪዎችና መንግስት ምርቶቻቸውን በመግዛት ድጋፍ እንዳደረጉላቸው አስታውሳ፣ ይህም በቀጣይ አገልግሎታቸውን ለማሻሻል እንደሚያግዛቸው አስረድታለች። በጊኖ ቀበሌ በስምንት ወጣቶች የተቋቋመውና በመስኖ እርሻ ሥራ የተሰማራው የሀዊ ጉዲና ማህበር ተጠሪ ወጣት መስፍን አያና በበኩሉ ካለፈው ዓምት አጠቃላይ ምርት ሽያጭ ከ15ዐ ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግሯል፡፡ ማህበሩ በብድር ያገኘውን 105 ሺህ ብር መልሶ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ወደ 2ዐዐ ሺህ ብር ማሳደጉን የጠቀሰው ወጣቱ አባላቱም በነፍስ ወከፍ በወር ከ2ሺህ እስከ 5ሺህ ብር እንደሚያገኙ ተናግሯል። ማህበሩ ከተቋቋመ ሁለት ዓመት እንደሆነው የገለጸው ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ሌሎች ወጣቶችን በመስኖ እርሻው በማሳተፍ የሚያመርተውን አትክልት ለሆቴሎችና ለዩኒቨርሲቲዎች በማቅረብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። የግራር ጃርሶ ወረዳ ኢንተርኘራይዝና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ቶልቻ ወደሥራ የገቡ ወጣቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር አካላት ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ተናግረዋል። "በእዚህም ወጣቶቹ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ ከመሆን አልፈው የወሰዱትን ብድር ከ7ዐ በመቶ በላይ ለመመለስ ችለዋል" ብለዋል። በዞኑ ባለፈው ዓመት በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ 38ሺህ 7ዐዐ ወጣቶች እራሳቸውን እንዲችሉ ከ300 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ብድር እንዲሁም የእርሻና የንግድ ቦታ እንደተሰጣቸው የጠቆሙት ደግሞ የዞኑ ኢንተርኘራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ኃይለማርያም ናቸው። በዘንድሮ ዓመት 41ሺህ ወጣቶችን በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች ለማሰማራት 5ዐዐ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ብድር፣ ስልጠናና መስሪያ ቦታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ባለፉት አራት ወራትም 16ሺህ ወጣቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል። በተለይ ወጣቶቹ ሥራን ሳይንቁ ተደራጅተውና ተባብረው እንዲሰሩ ለማድረግ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በዞኑ 13 ወረዳዎችና ከተሞች 81ሺህ የሚጠጉ ወጣቶች በሥራ አጥነት እንደተመዘገቡም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።