የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው በዋሺንግተን ዲሲ በሚካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ወደ ስፍራው ያቀናሉ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው በዋሺንግተን ዲሲ በሚካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ወደ ስፍራው ያቀናሉ
ጥቅምት 24/2012 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው አሜሪካ ከነገ በስቲያ በጠራችው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ማምሻውን ወደ ዋሺንግተን ዲሲ ያመራሉ። የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ስቴቨን ሙንቺን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ አገራቱን ለማወያያት ለኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ግብዣ አቅርበው ነበር። ስቴቨን ሙንቺን ባቀረቡት ግብዣ መሰረትም የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከነገ በስቲያ በአሜሪካ ርዕሰ መዲና ዋሺንግተን ዲሲ በሚካሄደው ውይይት ላይ ይሳተፋሉ። በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ዛሬ ማምሻውን ወደ ዋሺንግተን ዲሲ እንደሚያቀኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ ገልጸዋል። ከነገ በስቲያ በሚካሄደው ውይይትም አሜሪካ ሶስቱ አገራት በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን አቋም ለመስማት የጠራችው እንደሆነ ገልጸዋል። በግብጽ መገናኛ ብዙሃንና በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃኗ "ድርድር ነው እየቀረበ ያለው በሚል የሚቀርበው ዘገባ ስህተት" እንደሆነ ጠቅሰው የዋሺንግተን ዲሲው ውይይት አገራቱ በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን አቋም የሚገልጹበት ነው ብለዋል። የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ስቴቨን ሙንቺን ጥሪ ያደረጉት ለሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ብቻ እንደሆነና የቴክኒክ ጉዳዮች የውይይቱ አጀንዳ እንዳልሆነም አመልክተዋል። ኢትዮጵያም በውይይቱ ላይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን አቋም እንደምታቀርብና የተቋረጠው የሶስቱ አገራት የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ እንዲቀጥል በተደጋጋሚ እያንጸባረቀች ያለውን አቋሟን ለአሜሪካ ትገልጻለች ብለዋል። የዋሺንግተን ዲሲው ውይይት ኢትዮጵያ ለአሜሪካ በግድቡ ዙሪያ ያላትን አቋም ለማስረዳት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላትም ነው አቶ ነቢያት ያስረዱት። "አሜሪካ የህዳሴ ግድቡ ጉዳዮች በቴክኒክ ኮሚቴው ስብሰባ ምላሽ እንዲያገኙ ብታበረታታ የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው" ሲሉም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም በጽህፈት ቤታቸው ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር መወያያታቸው ይታወሳል። በውይይታቸው ወቅትም የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የተመለከቱ ጉዳዮች በቴክኒክ ኮሚቴው የጥናት ግኝት መፈታት እንዳለባቸው መግለጻቸው አይዘነጋም። በግንባታው ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች በቴክኒክ ኮሚቴው ግኝት መፈታት እንደሚችሉ ከኢትዮጵያ ጋር መግባባታቸውንም ገልጸው ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ኢትዮጵያና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ የተለያየ አቋም እንደሌላቸውም አመልክተዋል። ግብጽ በዋሺንግተን ዲሲው ጉዳይ ላይ የቴክኒክ ጉዳዮችን ጥያቄዎች ብታቀርብ የኢትዮጵያ ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል? በሚል ኢዜአ ለቃል አቀባዩ ጥያቄ አንስቷል። "የቴክኒክ ጉዳዮች የሚታዩበት የራሱ የሆነ መደበኛ መድረክ እንዳለና የቴክኒክ ጉዳዮች በቴክኒክ ኮሚቴው ስብሰባ ብቻ እንደሚታዩ ለአሜሪካ ታሳውቃለች" ሲሉ ነው አቶ ነቢያት ምላሻቸውን የሰጡት። በሩሲያ ሶቺ ከተማ ጥቅምት 12 እና 13 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደው የመጀመሪያው የሩሲያ አፍሪካ የኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፋታህ አልሲሲ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል። በውይይቱም የአገራቱ መሪዎች የቴክኒክ ኮሚቴው ስብሰባ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ እንደደረሱም አውስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዋሺንግተን ዲሲው የፖለቲካ ውይይት የቴክኒካል ኮሚቴ ስራውን የሚያደናቅፍ እንደማይሆን ከሶቺው ውይይት በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጻቸው የሚታወስ ነው።