ቀጥታ፡

በዞኖቹ በዘመቻ የታገዘ የአንበጣ መቆጣጠር ሥራ እየተሰራ ነው

ደሴ (ኢዜአ) ጥቅምት 24 ቀን 2012ዓ.ም---በደቡብ ወሎ ዞን በሦስት ወረዳዎች በ1ሺህ 500 ሄክታር ሰብልና እጽዋት ላይ የተከሰተን የአንበጣ መንጋ በዘመቻ የመቆጣጠር ስራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። የአንበጣ መንጋው ከሳምንት በፊት በቃሉ፣ አርጎባና ወረባቦ ወረዳዎች መከሰቱ ተነግሯል። የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት በተለይም በቃሉ ወረዳ በ400 ሄክታር ሰብልና እፅዋት ላይ የተከሰተን የአንበጣ መንጋ ከትላንት በስቲያ ጀምሮ በዘመቻ የመቆጣጠር ስራ እየተካሄደ ነው ። የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪዎች፣ የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት፣ የደጋን ከተማ ነዋሪዎችና የመንግስት ሠራተኞችን ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በዘመቻው እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል ። አቶ አሊ አንዳሉት የወረዳው መልከዓ ምድር አቀማመጥ በባህላዊ መንገድ እየተደረገ ያለውን የመቆጣጠር ስራ አስቸጋሪ ያደረገው በመሆኑ በአውሮፕላን በመታገዘ የኬሚካል ርጭት ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ነው። በአርጎባና ወረባቦ ወረዳዎችም አርሶ አደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በባህላዊ መንገድ እየተደረገ ያለው የመቆጣጠር ስራ መቀጠሉን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አስታውቀዋል ። በቃሉ ወረዳ የቀበሌ 21 ነዋሪ አርሶ አደር ኡመር አህመድ በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ያለሙት የደረሰ የማሽላ ሰብል ከግማሽ በላዩ በአንበጣ መንጋ መውደሙን ተናግረዋል ። ተማሪዎች፣ የመንግስት ሠራተኞችና የልዩ ኃይል ፖሊሶች መንጋውን ከማሳቸው ለማስወገድ እያደረጉላቸው ያለው ድጋፍ የቀረውን ሰብል ለማዳን ተስፋ ሰጭ መሆኑን ገልጸዋል ። “በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ ያለማሁት የደረሰ የማሽላ ሰብል በአንበጣ እየተበላብኝ ነው” ያሉት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ሀዋ ሰይድ ናቸው። ተማሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መንጋውን ከማሳቸው ላይ ለማጥፋት እያደረጉ ያለው ጥረት ወገናዊነትን ያሳየ መሆኑን የገለጹት አርሶ አደሯ፣ አንበጣውን ለማስወገዱ ሥራው በኬሚካል ርጭት ቢታገዝ የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም