ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንን አገር ለመበጥበጥ የሚሰሩ ሚዲያዎች ላይ እርምጃ አልወሰድክም በሚል ኮነነ

ጥቅምት 24/2012 የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የሕግ መስመር እየጣሱ ሁከትና ብጥብጥ በሚያስተጋቡ ሚዲያዎች ላይ እርምጃ አልወሰደም በሚል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኮነነ። ባለስልጣኑ በቀጣይ የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ ከመውደቁ በፊት ሚዲያዎችን አደብ እንዲያስገዛም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል። የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንን የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጦ፣ ግብረ መልስ ሰጥቷል። የቋሚ ኮሚቴው ግብረ መልስ የአባላቱ ጥያቄዎችም በድክመት ያነሳው ቁልፍ ነጥብ አገራዊ ለውጡ የፈጠረውን ነጻነት መገናኛ ብዙሃኑ በአግባቡ አልተጠቀሙበትም፣ ከዛ ይልቅ ሚዲያዎች የፖለቲካ ትግል መሳሪያ ሆነዋል የሚል ሃሳብ ላይ አተኩሯል። በተለይም አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን አገራዊ ሰላም፣ አብሮነትን፣ አንድነትን ለማጎልበት ከሚጠበቅባቸው ህዝባዊ ሃላፊነት ይልቅ፣ የአገር ህልውናን የሚፈታተን እርስ በርስ ግጭት፣ ብጥብጥ፣ መቃቃር በሚፈጥሩ ስራዎችን እያስተጋቡ መሆኑን ገልጿል። በዚህም ባለስልጣኑ በጥናትና ምርመር መረጃ ላይ ተመስርቶ ቀይ መስመር በተላለፉ መገናኛ ብዙሃኑን የማረምና ስርዓት የማስያዝ ሃላፊነቱን ለምን አልተወጣም ሲሉም ጠይቀዋል። በቴሌቪዥንና ሬዲዮኖች ስራ ክትትል ስራዎች 16 የሕግ ጥሰቶች እንደተገኙ በሪፖርቱ ቢጠቀሰም፣ ጥሰቶችና ግድፈቶች እንዳልታረሙና የችግሩ ምንጭ የሆኑ ሚዲያዎች ላይም እርምጃ አለመወሰዱን ቋሚ ኮሚቴው ኮንኗል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንዳሉት በተለይም በክልሎች መካከል ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን አጠቃላይ መልክ ግራ የሚያጋባ፣ አክቲቪዝም እና ጋዜጠኝነት የተቀላቀለበት፣ ከሙያዊ ስነ ምግባሩ ያፈነገጠ እንደሆነ አምነዋል። የባለስልጣኑ አደረጃጀት ሚዲያዎችን በተገቢው ሁኔታ ተከታትሎ ተጠያቂ ለማድረግ በሕግ የተሰጠው ኃላፊነትም ውስንነት እንዳለውና ተቋማዊ አቅምም የተገነባ አለመሆኑን አስረድተዋል። ለአብነትም በአዋጅ የተሰጠው በአብዛኛው አስተዳደራዊ እንጂ መክሰስ፣ ማስቀጣትና በህግ ተጠያቂ ማድረግ የሌላ ተቋም ሃላፊነት መሆኑን አንስተዋል። አሁን ላይ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅና የሚዲያ ፖሊሲ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፎች ሲጸድቁ፤ የሚጠበቀውን ሃላፊነት ለመወጣት እንደሚያግዝ አስረድተዋል። ባለስልጣኑ ችግሩን ለመፍታት ሙያዊ አቅምን ማጠናከር፣ ከሚዲያ ካውንስሉ ጋር መምከር፣ ህብረተሰቡ ስለሚዲያዎች ያለውን ስሜት የሚያስተጋባበት መድረክ ሲያዘጋጅ መቆየቱን ገልጿል። በጎ የሚሰሩትን ማበረታታት እንዳለ ሁሉ በህዝቦች መካከል ጥላቻን የሚዘሩ፣ ግጭት የሚቀሰቁሱና የአገር ህልውናን አደጋ ላይ የሚጥሉና ቅጥ ያጡ ሚዲያዎችን ግን ባለስልጣኑ እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል። ባለስልጣኑ እርምጃ መውሰድ ሲሞክር ለማስፈራራት የሚሞክሩ ወገኖች እንዳሉ ገልጸው፤ ወገንተኛ እንዳይመስል፣ፖለቲካዊ አረዳድ እንዳይኖር፣ ጥንቃቄ በተሞላበትና በሆደ ሰፊነት እንዲሁም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አጥንቶ ተጠያቂ ለማድረግ እንደዘገየ ገልጸዋል። ህብረተሰቡ አማራጭ ሚዲያዎች ማጣቱ ጉዳት እንዳለው ገልጸው፤ ያም ሆኖ ግን ከህግ ውጭ የሚንቀሳቀሱትን ተቋማት በወጣው ሕግ መሰረት ጣቢያ እስከመዘጋት ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል። በረቂቅ የሚዲያ ፖሊሲና አዋጅም በሁሉት ወራት ወስጥ እንደሚጸድቁ ግምታቸውን ገልጸው፤ ከሚዲያ ሕጉ በፊት ፖሊሲው እንዲቀድም ግፊት እያደረግን ነው ብለዋል። ቋሚ ኮሚቴው ግን ባለስልጣኑ አቅም ግንባታ፣ የሙያ ስነ ምግባር በሚል ብቻ ሳይወሰን ሆደ ሰፊነቱ ገደብ ኖሮት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድና ቀይ መስመር የሚጥሱ ሚዲያዎችን አደብ ማስገዛት አለበት ሲል አሳስቧል። በሌላ በኩል ከተቋሙ 161 ሰራተኞች መካከል ከባለስልጣኑ ስራዎች ጋር በተያያዘ ያሉት ሰራተኞች ከ50 እንደማይበልጡና ተቋሙ በብዛትም፣ በጥራትም የሰው ሃይል እጥረት እንዳለበት አስታውቋል። ከዚህ በፊት ተቋሙ ሁሉንም መገናኛ ብዙሃን ተከታትሎ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የመረጃ ስብሰባና ትንተና ስራዎች እንዳልነበሩት የባለስልጣኑ የስራ ሃላፊዎች ተናግረዋል። ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን የሚዲያ ክትትልና የይዘት ትንተና ስራዎች እንዲሁም ለሚዲያዎች የሚሰጠው ግብረ መልስ እየተሻሻለ መሆኑን ተጠቅሷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም