ቀጥታ፡

የማዕድን ኃብትን በአግባቡ ለመጠቀምና ለማስተዳደር የሚያስችል የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ተዘጋጀ

ጥቅምት 24/2012 ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ኃብት በአግባቡ ለመጠቀምና ለማስተዳደር ያስችላል ተብሎ የታመነበት የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ማዘጋጀቱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ። እቅዱ በአግባቡ ሥራ ላይ ከዋለ በመጪዎቹ አስር ዓመታት የማእድን ዘርፉ የአገራዊው ምጣኔ ኃብት ድርሻ አስር በመቶ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል። ኢትዮጵያ በርካታ ማዕድን ኃብት ያላት አገር መሆኗ ይነገራል። በተለይም የአገሪቱ የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ኃብት ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ትግል በአሸናፊነት ለመውጣት የሚያስችል አቅም መሆኑን ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚገልፁት። ሆኖም ይህ ኃብት ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ዘርፍ በአጠቃላዩ አገራዊ የምጣኔ ኃብት አፈፃፀም ውስጥ ያለው ሚና ከአንድ በመቶ በታች ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት የማእድን ኃብትን በአግባቡ በመጠቀም ለአገራዊ እድገት የበኩሉን እንዲጫወት የሚያስችል ትኩረት አለመሰጠቱ መሆኑ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የዘርፉን የ10 ዓመት መሪ እቅድ አስመልክቶ ዛሬ በጠራው ውይይት ላይ ተመልክቷል። ባለኃብቶች በዘርፉ ልማት እንዲሰማሩ የሚያስችሉ ምቹ የአሰራር ስርዓት አለመኖርም ሌላው በውይይቱ ላይ የተነሳ የዘርፉ ማነቆ ነው። ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የተዘጋጀው ረቂቅ እቅድ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን ሃብት በአግባባ እንድትጠቀም፣ እንድታስተዳድርና ለምጣኔ ኃብቱ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ያግዛል። ዶክተር ሳሙኤል እንዳሉት ለግብርና ብቻ ትኩረት ይሰጥ የነበረው ያለፉት ዓመታት የአገሪቱ የምጣኔ ኃብት መርሃ ግብር ለማዕድን የሰጠው ትኩረት እምብዛም ነው ብለዋል። ሆኖም በአሁኑ ወቅት የተያዘው የመንግስት የምጣኔ ኃብት መርሃ ግብር ሌሎች አማራጮችን ተጠቅሞ አገርን ማልማት ላይ ትኩረት በመሰጠቱ ዘርፉን ለማሳደግ ሰፊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ነው ያሉት። በዘርፉ የተፈጥሮ ልማት አስተዳዳር፣ በፈቃድ አሰጣጣጥ፣  የስነ ምዳር መረጃ አሰጣጥ ላይ የነበረው ክፍተት ባለሃብቶች በዘርፉ የመሳተፍ ፍላጎታቸው አነስተኛ አድርጎት እንደነበር ጠቁመዋል። በመጪዎቹ አስር ዓመታት አሁን የኮንትራት ውል የፈጸሙ ኩባንያዎችን ታሳቢ በማድረግ ወደ20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት እቅድ ተነድፏል ብለዋል። ዘርፉ ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥርና 100 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች እንደሚቋቋሙ ታሳቢ መደረጉን አስታውቀዋል። ይህንን ጥቅል ምጣኔ ኃብታዊ መነሻ በማድረግ በመጪዎቹ አስር ዓመታት ዘርፉ ለአገራዊው የምጣኔ ኃብት የሚኖረውን ድርሻ ወደ 10 በመቶ ለማድረስ ትልም መያዙንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ረቂቅ እቅዱ የተዘጋጀው በሚኒስቴሩ የተቀረፁትን የማዕድንና የነዳጅ ስራዎች ፖሊሲ መሰረት በማድረግ መሆኑንም ጠቁመዋል። ላለፉት ስድስት ወራት ሲዘጋጅ የቆየው ረቂቅ ዕቅዱ ከተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በሚካሄዱ ውይይቶች እንዲዳብር ተደርጎ ወደተግባር ይለወጣል ሲሉም ገልፀዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ ተወካይ ሚስተር ኦሎቨር ቺንጋኒያ እንዳሉት መሪ እቅዱ መዘጋጀቱ ሀገሪቱ ያላትን ሃብት በአግባባ ለመጠቀም ትልቅ ዕድል ይፈጥርላታል። ዕቅዱ ዘርፉ አሁን እያበረከተ ካለው አነስተኛ ገቢ ወጥቶ አስተዋፅኦውን እንዴት ማሳደግ ይቻላል የሚለውን በሰፊው የዳሰሰ በመሆኑ ለኢትዮጵያ መንግስት ትልቅ አጋጣሚ እና እድል ነው ማለት ይቻላል ብለዋል። ሌሎች የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ እያዘጋጀች ባለው የ10 ዓመት እቅድ ትልቅ ተመክሮ ሊወስዱ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል። አፍሪካውያን ራሳቸውን የተፈጥሮ ሀብት በራሳቸው አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል ብርቱ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውን አሳስበዋል። በውይይቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በኢኮኖሚ ጉዳይ የሚሰሩ አካላት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የሲቪል ሶሳይቲ ተወካዮች፣ ሌሎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ይፋ ያደረገው አገር በቀል የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ መርሃ ግብር ትኩረት ከሰጣቸው ስምንት የልማት ዘርፎች መካከል አንዱ ማእድን ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም