ቀጥታ፡

ለማኀበራቱ በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም እየተዘረጋ ነው

አዳማ (ኢዜአ) ጥቅምት 24 ቀን 2012 የገንዘብ፣ ቁጠበና ብድር ኀብረት ሥራ ማህበራትን አሠራር ለማዘመን በአገሪቱ በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን የፌዴራል ኀብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ባለፉት 12 ቀናት በአዳማ ከተማ ሲሰጥ የቆየው የገንዘብ፣ ቁጠበና ብድር ኀብረት ስራ ማህበራት የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የአሰልጣኞች ስልጠና ተጠናቋል።

በዚህ ወቅት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲ ሙመድ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት በአገሪቱ የሚገኙ የገንዘብ ቁጠበና ብድር ኀብረት ሥራ ማህበራት በርካታ ማነቆዎች አሉባቸው።

ከነዚህ ውስጥ ዋነኛው በማኔጅመንት ሲስተም የመጠቀም ውስንነት መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታት አሰራራቸውን ማዘመን ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በዚህ ረገድ በፓይለት ፕሮጀክት ደረጃ ከኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ትግራይና ቤንሻንጉል ክልሎች ውስጥ ለተመረጡ 50 ዩኒየኖች የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም እየተዘረጋላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከዓለም አቀፍ ፈንድ ለግብርና ልማት በተገኘ 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መገኘቱንና ሥራው በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ሲስተም የመዘርጋት ሥራውን እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ በማጠናቅቅ ዩኒየኖቹን ተጠቃሚ ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

እንደ አቶ አብዲ ገለጻ የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም መዘርጋቱ የኀብረት ሥራ ማህበራቱን አሰራር የተንዛዛ እንዳይሆን ከማድረግ ባሻገር ፈጣን አስተዳደራዊ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ነው።

"ከእዚህ በተጨማሪ  በየደረጃው ለሚገኘው አርሶና አርብቶ አደሮች ተደራሽ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይረዳል" ብለዋል።

የሶፍት ዌር ዴቬሎፐር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ገሰሰ በበኩላቸው የሕብረት ሥራ ኤጀንሲው በገዛቸው 50 ከፍተኛ ሰርቨሮች ላይ ሲስተሙ በመጫን ላይ መሆኑን ነው የገለጹት።

ከዩኒየኖች ለተውጣጡ 50 ሥራ አስኪያጆችና የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በሲስተሙ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ስልጠና መሰጠቱንና ዩኒየኖቹም በቅርቡ መጠቀም እንደሚጀምሩ አስረድተዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የኮኮብ ገንዘብ፣ ቁጠበና ብድር ኀብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ገበያው ውድነህ አንዱ ናቸው።

"የኢንፎርሜሽን ማኔጅመንት ሲስተሙ ዘመናዊ የመረጃና ሒሳብ አያያዝ፣ የንብረትና የሰው ኃይል አስተዳደር ሥርዓትን በአንድ ሶፍትዌር ለመምራት እንደሚያስችል በስልጠናው ግንዛቤ አግኝተናል" ብለዋል።

ይህ ደግሞ የዩኒየኑን አሠራር በከፍተኛ ሁኔታ በማዘመን ለአባላቱ ቀልጣፋና ግልጽ አሰራር ለመዘርጋት እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።

ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው 20 ሺህ መሠረታዊ ሕብረት ሥራ ማህበራት የሚገኙ ሲሆን ከ20 ሚሊዮን ለሚበልጡ አርሶና አርብቶ አደሮች የብድር አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም