ለ2021 ለአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ዋልያዎቹ ልምምዳቸውን ነገ ይጀምራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ለ2021 ለአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ዋልያዎቹ ልምምዳቸውን ነገ ይጀምራሉ
ጥቅምት 23/2012 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2021 ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ለሚያደርገው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ነገ በትግራይ መቀሌ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ልምምዳቸውን ይጀምራሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ከማዳጋስካር አቻው ጋር የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። ለዚህም የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል። ከእነዚህም መካከል 20ዎቹ በአገር ወስጥ ከተለያዩ ክለቦች የተውጣጡ ሲሆኑ ከአገር ውጪ ባሉ ሊጎች የሚጫወቱት ሽመልስ በቀለ፣ ጋቶች ፓኖም እና ቢንያም በላይ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ናቸው። ከተጠሩት 25 ተጫዋቾች መካከል በወዳጅነት ጨዋታዎችና በቻን ማጣሪያ የመጀመሪያ ተሰላፊ የሆነው የብሔራዊ ቡድቡና የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ግብ ጠባቂ ለአለም ብርሃኑ ከክለቡ ጋር በቅድመ ዝግጅት ልምምድ ላይ ጉዳት አጋጥሞታል። በዚህም ተጫዋቹ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ከብሄራዊ ቡድኑ ስብስብ ውጪ ሲሆን በምትኩ የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ጥሪ አንደተደገለት ታውቋል። በቅርቡ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መቀመጫዋ ግብፅ ካይሮ ላይ በወጣው የምድብ ማጣሪያ ግጥሚያዎች በምድብ 11 ኢትዮጵያ ከማዳጋስካር፣ ኮትዲቯርና ኒጀር ጋር መደልደሏ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑ ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ማዳካስካር ተጉዞ አንታናናሪቮ ላይ የምድብ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን የማዳካስካር ብሔራዊ ቡድንን የሚገጥም ይሆናል። ህዳር 9 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ በመቀሌ ስታዲየም ከአይቮሪኮስት አቻው ጋር የምድቡን ሌላኛው ጨዋታ ያደርጋል። የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ በምዕራብ አፍሪካዋቷ ካሜሩን አስተናጋጅነት የሚደረግ ነው የሚሆነው። ይህም 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሆን በምድብ ማጣሪያውም 12 ምድቦች የሚገኙ ሲሆን፤ የየምድቦቹ 1ኛ እና 2ኛ ቡድኖች የአፍሪካ ዋንጫው ተሳታፊ ይሆናሉ። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በፊፋ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ መሰረት ከዓለም 211 አገራት 150ኛ፤ ከአፍሪካ 54 አገራት ደግሞ 44ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ ትገኛለች፡፡