ህብረተሰቡ የተሻለ የፓስፖርት አገልግሎት የሚያገኝበት የአሰራር ስርአት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ የተሻለ የፓስፖርት አገልግሎት የሚያገኝበት የአሰራር ስርአት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል
አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2010 ለህብረተሰቡ የፓስፖርት አገልግሎትን በተሻለ መልኩ ለማቅረብ ያስችላል ተብሎ የታመነበት የአሰራር ስርአት (ሲስተም) ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ የዘረጉት የአሰራር ስርአት ፓስፖርት በማግኘት ሂደት ውስጥ የተገልጋይ መረጃ ምዝገባ፣ የክፍያና የቀጠሮ መስጫ ጊዜ ህብረተሰቡ የሚያጋጥመውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለማቃለል የታሰበ ነው ተብሏል። ሁለቱ አካላት ስርአቱ በዛሬው ዕለት ወደ ስራ መግባቱን አስመልክተው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ በጋራ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ የፓስፖርት አገልግሎት ስርአቱ በአዲስ አበባ በሚገኙ 30 የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች መተግበር እንደሚጀመር ጠቁመዋል። የተዘረጋው ስርአት ፓስፖርት ማውጣት የሚፈልጉ ዜጎች ለአገልግሎቱ ብቻ ተብለው በባንኩ ቅርንጫፎች በተዘጋጁ ቢሮዎች ምዝገባ ማከናወን እንደሚችሉ ተናግረዋል። ከምዝገባው በኋላ ተጠቃሚዎች ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ኢሚጊሬሽን በመሄድ አሻራ የሚሰጡበትንና ፎቶ የሚነሱበትን የቀጠሮ ቀን በባንኩ ከሚሰሩ ሰራተኞች ማወቅ እንደሚችሉም አስረድተዋል። ዜጎች ፓስፖርት ለማውጣት የሚከፍሉትን ገንዘብ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በቀላሉ መክፈል ይችላሉ ብለዋል። አሰራሩ ገንዘብ ለመክፈል የነበረውን ምልልስ በማስቀረት የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ነው አቶ በቃሉ ያብራሩት። በአጠቃላይ ሁሉም አገልግሎቶች ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚከናወኑ በመሆናቸው የኢሚግሬሽን አገልግሎት ፈላጊዎችን በተቀላጠፈና በተቀናጀ መልኩ በማስተናገድ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን እንዲቆጥቡ በእጅጉ እንደሚረዳ ጠቅሰዋል። የአሰራር ስርአቱ ላለፈው አንድ ወር በተወሰኑ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች የሙከራ ትግበራ ላይ እንደነበር አስታውሰው በአጠቃላይ የአሰራር ስርአቱን ከአዲስ አበባ ውጪ ተደራሽ ለማድረግ በክልል በሚገኙ ቅርንጫፎች አገልግሎቱ እንደሚሰጥ አመልክተዋል። ባንኩ ለህብረተሰቡ ካለው ሰፊ ተደራሽነት አንጻር የአሰራር ስርአቱን በጋራ በመተግበሩ አገልግሎቱን በተሻለ መልኩ ለመስጠት ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል ነው ያሉት አቶ በቃሉ። የአሰራር ስርአቱን መተግበር ከመጀመሩ በፊት ለባንኩ ሰራተኞች ስልጠና እንደተሰጠና ለስራው የሚያስፈልግ የቴክኖሎጂ አቅርቦት እንዲሟላ መደረጉን ገልጸዋል። የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ገብረዮሐንስ ተክሉ በበኩላቸው የመምሪያውን አገልግሎት ለማግኘት በቀን ከአንድ ሺህ እስከ ሰባት ሺህ ዜጎች ወደ ተቋሙ ስለሚመጡ ተገልጋዮች ለእንግልትና ለጊዜ ብክነት መዳረጋቸውን ገልጸዋል። 'ይፋ የተደረገው የአሰራር ስርአት የተቋሙን አገልግሎት በፍጥነትና በአጭር ጊዜ ለመስጠት ያስችላል' ብለዋል። ስርአቱ የተዘረጋው በሁለቱ ተቋማት በሚገኙ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በመዘጋጀቱ የገንዘብ ወጪውን ማዳን እንደተቻለ ጠቁመዋል። ዜጎች ፓስፖርታቸውን በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ቅርንጫፎች ማግኘት የሚችሉበት አሰራር ተግባራዊ እየሆነ መሆኑን ገልጸው 'ይህም ዜጎች አስር ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ፓስፖርታቸውን ማግኘት እንዲችሉ በማድረግ ያለውን ወረፋ እየቀነሰ ነው' ብለዋል። የአሰራር ስርአት መተግበሩ የመንግስት ተቋማት ተናበውና ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው የሚያሳይ መልካም ጅምር እንደሆነ አቶ ገብረዮሐንስ አስረድተዋል። በሌላ በኩል 'በአዲስ አበባና በክልል የሚሰጠው ፓስፖርት የተለያዩ ናቸው' በማለት የሚያታልሉ ደላላዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ሁሉም ቦታ የሚሰራው ፓስፖርት ተመሳሳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል። የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በድሬዳዋ፣ ሃዋሳ፣ ጅማ፣ ባህርዳር፣ ደሴና መቀሌ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነና በቀጣይም በአዳማ፣ በጅግጅጋ፣ ሰመራና አሶሳ ቅርንጫፍ ለመክፈት እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።