ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃኑ በሀገሪቱ የሚፈጠሩ ግጭቶችን እያባባሱ ነው - የዘርፉ ባለሙያዎች

ኢዜአ፤ ጥቅምት 23/2012 መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነምግባርን ጠብቀው ከመስራትና ማህበረሰቡን ከማስተማር ይልቅ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን እያባባሱ መሆኑን ባለሙያዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በበኩሉ መገናኛ ብዙሃኑ የሚሰሯቸውን የዘገባ ስህተቶች እና አባባሽ ይዘቶች እንዲያስተካክሉ በቃልና በደብዳቤ እያሳወቅኩ ነው ይላል።

ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚፅፉት በፍቃዱ ኃይሉ“የክልል መገናኛ ብዙሃን ወገንተኝነት እና ለገዥው ቡድን አጎብዳጅነት” እንደሚታይባቸው አንስተው፤ ብዙ ፖለቲካዊ ዘገባዎችን እና ትርክቶችን በተዛባ መልኩ የሚያቀርቡ እንደሆኑ ነው የገለጹት።

ዘውግ ተኮር የሆኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሙያዊ ስነምግባርን ጠብቀው ያለመዘገብ፣ ሀቅን እንዳለ ያለማቅረብና ሚዛናዊ አለመሆን እንደሚስተዋልባቸው የሚናገሩት ጸሐፊው፤ ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ግጭት በሚስተዋልበት ወቅት የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እንዳይዘግቡ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።

አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ስህተት የሚፈጽሙት ባለማወቅ  መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አይነት ስህተት እንዲወጡ መጀመሪያ በማስተማር የተለየ ሁኔታ ሲያጋጥም በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባልም ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ የህዝብ ማስተማሪያ አልያም የጦር መሳሪያ የመሆን እድል ስላላቸው ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሀሳባቸውን በመስጠት፤ የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለሥልጣልም የበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ  ጠቁመዋል።

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር ና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ  የሶስተኛ ድግሪ ተማሪ ሃይማኖት ጌታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ “ፅንፍ ይዞ እየተጓዘ” መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለግጭት አባባሽ እየሆነ ነው ይላሉ።

በተለይ አንዳንድ “የፅንፍ ፖለቲካ” የሚያራምዱ ግለሰቦች የራሳቸውን መገናኛ ብዙሃን በመክፈት የሚፈልጉትን “ፅንፈኛና የጥላቻ አጀንዳ” እያሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል።

በመንግስት ሚዲያ በኩል ደግሞ “ህዝብ ሲሞት እና ጉዳት ሲደርስበት ተከታትሎ ከመዘገብና መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ መንግስትን እየጠበቁ የመዘገብ አዝማሚያ ይታይባቸዋል” ነው ያሉት።

መገናኛ ብዙሃኑ አስቀድመው የስጋት ትንተናዎችን በሚዛናዊነት በማቅረብ ግጭትን የመከላከል ሚና እየተወጡ አይደለም  ያሉት  መምህር ሃይማኖት፤ ብሮድካስት ባለስልጣንም ለመገናኛ ብዙሃኑ የተሰጣቸው ነጻነት እንዳይታፈን ጥንቃቄ  በማድረግ፤  በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ ባሉት ላይ የእርምት እርምጃ  ሊወስድ ይገባል ብለዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ  ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደወሰን አንዱዓለም “የሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ በተረበሸ ቁጥር መገናኛ ብዙሃኑም አብረው መታመማቸው ከፍተኛ ችግር አስከትሏል” ነው ያሉት።

አብዛኛው መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ከህዝብ፣ ክልልን  ከክልል፣ መንግስትን ከህዝብ የሚያራርቁ ዘገባዎችን እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለህዝብ የሚጠቅሙ ማህበራዊ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎች  የህይወት መልኮችን ትተው ፖለቲካ  ላይ ብቻ የመጠመድ ችግር ይታይባቸዋል ነው ያሉት።

ባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙሃኑን ስራዎች መዝኖ እርምጃ ለመውሰድ ከዚህ ቀደም የነበረውን ፖለቲካዊ መስፈርት በመቀየር ሙያዊ መመዘኛ ማዘጋጀቱን ጠቁመው፤ በመስፈርቱ መሰረት ድክመትና ጥንካሬ ተለይቶ እንዲያስተካክሉት ለተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን ደብዳቤ መላክ መጀመሩንም ገልጸዋል።

“ሀገሪቱ ለውጥ ላይ ናት በሚል መገናኛ ብዙሃኑ የነውጥ አራጋቢ ሆነው እንዲቆዩ መፍቀድ አይገባም” ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ የፖለቲካ ሁኔታ በተረበሸ ቁጥር ሚዲያው አብሮ መረበሽ እንደለሌበት ና በቅርቡ በሚወጣው የመገናኛ ብዘሃን አዋጅ ግልፅ ድንበር  እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

የፖለቲካ አመራሮች በቦርድም ሆነ በሚዲያ መሪነት እንዳይሰየሙ በረቂቅ አዋጁ መቀመጡን አንስተው፤ መገናኛ ብዙሃኑ ከባለሥልጣኑ ጋር እንደ “አይጥና ድመት” ከሚተያዩ እርስ በራሳቸው የሚተራረሙበት፣ የሚነጋገሩበትና የሚደጋገፉበት የመገናኛ ብዙሃን ካውንስል መቋቋሙንም ነው የገለጹት።

“በልቅነት እየሰሩ ያሉትን ለማረም ሲባል በነጻነት ላይ ያሉት መጎዳት የለባቸውም” ያሉት አቶ ወንደወሰን፤ ችግሩን ለማረምና ሁለቱን ለመለየት ከውይይትና ከአቅም ግንባታ ጀምሮ በቀጣይ በህግ የተጠና  የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ችግር እየፈጠሩ ላሉ መገናኛ ብዙሃን በአካል እስከ ክልል ድረስ በመሄድ እንዲያርሙ የማወያየት፣ በደብዳቤ የማሳወቅ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸው፤ አሁን እስከተሄደበት ድረስ  ሚዲያዎቹ ካልታረሙ፤ በሀገሪቱ ህግ እና በብሮድካስት አዋጁ መሰረት የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም