ቀጥታ፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለበጎ ፍቃደኛ ክለቦች እውቅና ሰጠ

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 22ቀን 2ዐ12  ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በበጎ ፍቃደኝነት ለሚያገለገሉ ክለቦች ዛሬ እውቅና ተሰጥቷል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከተመሰረተ ጀምሮ በበጎ ፍቃደኝነት የሚያገለግሉ ወጣቶች በውድድሩ ወቅትና ከውድድሩ ውጪም የተለያዩ ስራዎችን ያግዛሉ። እነዚህ ወጣቶች ከተለያዩ የበጎ ፍቃደኛ ክለቦች የተውጣጡና በግለሰብ ደረጃም በፍቃደኝነት የሚሳተፉ ናቸው። በበጎ ፍቃድ ተግባር ለሚያገኙት እርካታ የሚሳተፉ እንዳሉ ሆነው ለተለያየ የበጎ አድራጎት ስራቸው  የገንዘብም ሆነ የሙያ ድጋፍ ሲፈልጉም ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያገኛሉ። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋናው ውድድር ሲካሄድ ከ350 ያላነሱ በጎ ፍቃደኞች ይካፈሉበታል። እነዚህ በተለያዩ የበጎ ፍቃደኛ ክለቦች የታቀፉ ወጣቶችና ከታላቁ ሩጫ ጋር እየሰሩ ያሉ ክለቦች ዛሬ እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ከክለቦቹ መካከል ሶሊያና ሮትራክት፣ ስካውት፣ እኛ ለእኛ እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ይገኙባቸዋል። ከሶሊያና ሮትራክት የመጣችው ቤተልሄም ሽፈራም ለኢዜአ እንደተናገረችው አቅመ ደካሞችን የማገዝ፣ ትምህርት ቤቶች የህፃናትን ቀልብ የሚስቡ እንዲሆኑ በስዕል የማስዋብ፣ እድሳት የማከናወንና የጽዳት ስራዎችን በበጎ ፍቃደኝት ይከውናሉ። በዚህ ተግባር በመሳተፍ የመንፈስ እርካታ ከማግኝት በተጨማሪ በእውቀትም አቅሟን ለማሳደግ እንዳገዛት ትናገራለች። ከተለያዩ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ እድል የሚፈጥር፤ ችግሮች ሲኖሩም ለመፍታት በጋራ እንደሚያሰራ ገልጻለች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት። ወጣት ስጦታው አዲስ በስካውት በጎ ፍቃደኞች ክለብ አባል ሲሆን የተቸገሩ ስዎችን ባላቸው አቅም ለመርዳት ቃል ገብተው ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ነው የተናገረው። ይህም ለራስ የሚሰጠው እርካታ እንዳለ ሆኖ በውስጡ የተለያዩ ስራዎች ሲያከናውኑ እውቀት ለማግኘት ትልቅ አጋጣሚን የሚፈጥር ነው ብሏል። በሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ባለቤትነት የሚመራው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ በጎ ፍቃደኝነት ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አስረድተዋል። እርሳቸው ታላቁ ሩጫን የተቀላቀሉት በበጎ ፍቃደኝነት እንደነበርና ያላቸውን እውቀት ለማዳበር እድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። በድርጅቱ በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ላይ ተመደበው ሲሰሩ እንደቆዩና በሂደትም የስራ አስኪያጅነት ደረጃን ማግኘታቸውን አውስተዋል። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ኦፕሬሽንና ኢቨንት ማናጀር አቶ ዳግም ተሾመም ስራውን በበጎ ፍቃደኝት እንደጀመሩና አሁን ላሉበት ኃላፊነት እንደበቁ ይናገራሉ። አቶ ዳግም በጎ ፍቃደኞች ከሚያገኙት የህሊና እርካታ ባሻገር ሙያ ለመልመድ ትልቅ ሚና እንዳለው በመግለጽ ለፍቃደኝት ስራ በጎ አመለከካትን ማዳበርና የመሳተፍ ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም