ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞች ቁጥር በሰባት እጥፍ አድጓል

ጥቅምት 22/2012 በሶማሊያ ባለው ድርቅና ግጭት ሳቢያ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ የአገሪቷ ዜጎች ቁጥር በሰባት እጥፍ ማደጉን የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የአገሪቱ ስደተኞች ቁጥር ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ሰባት እጥፍ መሆኑን ለኢዜአ ገልጿል። የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ያሲን አልይ እንዳሉት ኢትዮጵያ 7 ሺህ 800 የሶማሊያ ስደተኞችን በ2019 ተቀብላለች። በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ድርቅና ግጭት የሶማሊያ ዜጎች ከአገራቸው እንዲሰደዱ ያደረጉ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውንም ገልፀዋል። በ2018 ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የሶማሊያ ስደተኞች ቁጥር 1 ሺህ 101 የነበረ ሲሆን በ2019 ቁጥሩ ወደ 7 ሺህ 831 ከፍ ማለቱን መረጃዎች ያሳያሉ ነው ያሉት ኃላፊው። አልሸባብ በደቡብ ሶማሊያ የሚያሳድረው ጫና በአንድ በኩል፤ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ድርቅ በሌላ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሶማሊያዊያን ቁጥር እንዲያሻቅብ ማድረጉንም ያነሳሉ። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 263 ሺህ የሶማሊያ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ለስደተኞች በሯን ክፍት ማድረጓን ተከትሎ ኤጀንሲው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን ለስደተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ እያቀረበ መሆኑንም አስረድተዋል። አቶ ያሲን ኢትዮጵያ የስደተኞችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች መሆኗንም አንስተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት አንዳንድ ህጎችን በማሻሻል ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን በመጠቆም። በሊበን ዞን ዶላዶ ስደተኞች ካምፕ ስደተኞች በመስኖ ልማት እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑንና አንድ ሺህ ስደተኞች በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነፃ የትምህርት ዕድል እንዳገኙ አስረድተዋል። የደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪው መረሳ ካህሱ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶችና ኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይ መሆኗ የስደተኞች ቁጥር እንዲበራከት አድርጓል ይላሉ። አልሸባብ የአገሪቷን ከተሞችና መንደሮች ማጥቃቱም የሶማሊያ ስደተኞች የተሻለ ህይወትን በመሻት ወደ ኢትዮጵያ እንዲተሙ ማድረጉንም አክለዋል። የሶማሊያ የሠላምና መረጋጋት ችግር በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ኅብረትና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ባለፈው አንድ ዓመት እየረገበ ቢመጣም ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ900 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የኤርትራ፣ የየመንና የሶሪያ ስደተኞች በኢትዮጵያ ተጠልለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም