በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የተገነቡ ሆስፒታሎች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

75
ነቀምቴ ሰኔ 12/2010 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በ67 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ ሁለት ሆስፒታሎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የዞኑ ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት ገለፀ ። የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ሶሪ ለኢዜአ እንደገለፁት ግንባታቸው በ2005 ዓም ተጀምሮ አሁን ለአገልግሎት የበቁት የአቤ ደንገሮና የጉድሩ ሆስፒታሎች ናቸው ። ሁለቱም ሆስፒታሎች ለ200 ሺህ ህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው ብለዋል ። የሆስፒታሎቹ ግንባታ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በተቋራጮች አቅም ማነስና በህንፃ ግንባታ መሳሪያዎች ዋጋ መናር ምክንያት ለተጨማሪ ሶስት ዓመታት ተጓትተው በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ አሳድረው መቆየታቸውን ተናግረዋል ። አሁን ግን ለሆስፒታል የሚያስፈልጉ የህክምና ክፍሎችና የህክምና መስጫ መሳሪያዎች ተሟልተውላቸው ካለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አስረድተዋል ። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የአቤ ደንጎሮ ወረዳ የቱሉ ዋዩ ቀበሌ ነዋሪ  ወይዘሮ ዳዊ ዱጋሳ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው ሆስፒታል ባልነበረበት ወቅት አገልግሎቱን ፍለጋ ወደ ነቀምቴና ሆሮ በመሄድ ለከፍተኛ ወጪና እንድልት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል ። አሁን ግን በአካባቢያቸው የተገነባው ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ አቅመ ደካማውና ድሃው ህብረተሰብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዳደረገው ተናግረዋል ። አቶ አብርሐም አበበ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው የሆስፒታሉ መገንባት የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ የመለሰ ነው ። የጉዱሩ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዳባ ህርጳ እንዳሉት ደግሞ አካባቢው የትራንስፖርት ችግር የሚታይበት በመሆኑ የሆስፒታሉ መገንባት በወሊድ ወቅት ወላዶችን በቃሬዛ ተሸክመው ረጅም መንገድ በእግር ሲያደርጉት የነበረው ጉዞ አስቀርቶላቸዋል ። ከዞኑ ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የዞኑ የጤና ኬላና የጤና ጣቢያ ሽፋን 97 በመቶ የሆስፒታል ደግሞ 25 በመቶ ነው። ዞኑ በአሁኑ ጊዜ 3 ሆስፒታሎች ፣ 49 ጤና ጣቢያዎችና 178 ጤና ኬላዎች አሉት ተብሏል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም