የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የቀይ መስቀል ሰራተኞች ባለፈው ክረምት የተከሉትን የዛፍ ችግኝ ተንከባከቡ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የቀይ መስቀል ሰራተኞች ባለፈው ክረምት የተከሉትን የዛፍ ችግኝ ተንከባከቡ
ኢዜአ ጥቅምት 22/2012 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ሰራተኞች ባለፈው ክረምት የተከሉትን ችግኝ በዛሬው እለት ተንከባክበዋል። ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ቀን ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉ ይታወሳል። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የቀይ መስቀል ሰራተኞች በወቅቱ የተከሉትን ችግኝ ዛሬ እንክብካቤ አድርገዋል። ሰራተኞቹ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የተከሉትን ችግኝ የመኮትኮት፣ ውሃ የማጠጣትና አረም የማስወገድ ተግባር አከናውነዋል። በዚሁ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰራተኛ አቶ ዮሃንስ ወንድይራድ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ እንዲጸድቅ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። ''ችግኞቹ እንዲያድጉ እንክብካቤያችንን እንቀጥላለን'' ብለዋል። የቀይ መስቀል ሰራተኞችም በተመሳሳይ መልኩ የተከሏቸውን ችግኞች እስኪያድጉ ድረስ መንከባከባቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። የተቋሙ ሰራተኞች እንደገለጹት፤ ተቋሙ ባለፈው ክረምት 10 ሺህ ችግኝ የተከለ ሲሆን በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር ጭምር በዛሬው ዕለት የመንከባከብ ስራ ሰርቷል። በጉለሌ ክፍለ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ የአረንጓዴ ቦታዎች አያያዝና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ወንድወሰን ሽፈራው እንዳሉት፤ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ተገቢ እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል። በዓመት አራት ጊዜ እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል። በክፍለ ከተማው የተተከሉ ችግኞች እስከ አሁን 90 በመቶ የጽድቀት መጠን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። በቀጣይ የተጠናከረ እንክብካቤ ስለሚያስፈልግ የመንከባከቡ ስራ ትኩረት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል። ተቋማት ውል ገብተው የተከሉ በመሆኑ በውላቸው መጠን መንከባከብ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ''ብዙ ተቋማት እየተንከባከቡ ባለመሆኑ መጥተው የተከሉትን ሊንከባከቡ ይገባል'' ብለዋል። በመላው ኢትዮጵያ ባለፈው ክረምት ከአራት ቢሊዮን በላይ የዛፍ ችግኝ መተከሉ ይታወሳል።