ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ተመሰረተ

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 22 ቀን 2012 የኢትዮጵያ ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ዛሬ በይፋ ተመሰረተ።

ማህበሩ ዛሬ በይፋ የተመሰረተው አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደ የመመስረቻ ጉባኤ ላይ ነው።

ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ የቱሪዝም መስህብ ያላት አገር ብትሆንም ከዘርፉ እየተጠቀመች ያለው ግን እጅግ አነስተኛ መሆኑ በጉባኤ ላይ ተመልክቷል።

ቱሪዝም ለአገራዊው ምጣኔ ኃብት የሚገባውን ሚና ማበርከት እንዳይችል ካደረጉት አያሌ ምክንያቶች መካከል አንዱ ደግሞ በዘርፉ የሰለጠነን ባለሙያ በአግባቡ አለመጠቀምን ለአብነት በማንሳት።

እናም ይህ ከቱሪዝም ኢንደስትሪው ጋር በተያያዘ ሙያ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ያቀፈው ማህበሩ ዓላማ ዘርፉ ለአገራዊው ምጣኔ ኃብት እድገት የሚጫወተውን ሚና ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት በግንባር ቀደምነት ማገዝ ነው።

የሚስተዋሉትን ፈተናዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ለመፍታትና ዘርፉን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ከማህበሩ ዓላማዎች መካከል መሆኑን የምስረታው አስተባባሪ ኮሚቴ አባል አቶ ስለሺ ግርማ ገልፀዋል።

ከዘርፉ ልማት ጋር በተያያዘ በተበታተነ መንገድ የሚደረጉት ጥረቶችን በማቀናጀት፤  በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለመፍጠር የሚያስችል ድጋፍ ማድረግም የማህበሩ ዓላማ  ነው ብለዋል።

ሌላኛው የማህበሩ አስተባባሪ ኮሚቴ አቶ ቴዎድሮስ ደርበው በበኩላቸው "ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ለመንደፍና እንቅፋት የሚሆኑትን ደግሞ ለማስቀየር የሚያስችል በጥናትና ምርምር ላይ የተደገፈ ጫና ለመፍጠር የሙያ ማህበሩ ትልቅ ሚና አለው" ነው ያሉት።

የሙያ ማህበሩ ከሌሎች ጎረቤት አገሮችና ዓለማት የእውቀት ሽግግር በማድረግ ደረጃውን የጠበቀ የቱሪዝም ልማት ለመፍጠርና ከቱሪዝም መገኘት ያለበትን ገቢ ለማሳደግ፣ የቱሪዝም ልማቱንና ገበያውን ለማዘመን እንደሚረዳም አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።

ማህበሩ የቱሪዝም ልማቱን የሚያግዙ ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ፤ በየዓመቱን የምርምር መፅሄት የማሳተም ግብ መያዙም ተጠቁሟል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄደውን ጥናትና ዝግጅት ተከትሎ ዛሬ ይፋ የሆነው ማህበር መስራች ሆነው ያቋቋሙት ከ250 በላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ናቸው።

ግለሰብ የቱሪዝም ባለሙያዎችን ጨምሮ ከዘርፉ ጋር በተያያዘ ተግባር የተሰማሩ ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶችና የቱሪዝም ዘርፍ ተማሪዎች የማህበሩ አባል መሆን ይችላሉ።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶችንና የሆቴል ባለቤቶችን ጨምሮ ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ባላቸው የሥራ ዘርፎች ተመስርተው እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ማህበራት በማሰባሰብ ፌዴሬሽን የመመስረት ትልምም አለው ተብሏል።

በጉባኤው ላይ የተገኙ ባለሙያዎች በሰጡት አስተያየት ማህበሩ በተለይ ከከፍተኛ ትምሀርት ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት የሚፈጥርበትን መንገድ እንዲዘይድ ጠይቀዋል።

ማህበሩ አስፈላጊውን መስፈርት ካጠናቀቀ በኋላ በቅርቡ ወደሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም