የካራ ማራ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምግባ መርሃ ግብር ተቋረጠ

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 22 ቀን 2012 በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 የሚገኘው ካራ ማራ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር መቋረጡ ተገለጸ።

በዚህ ትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር ሊቋረጥ የቻለው በማህበራቱ የቅድመ ዝግጅት ማነስ መሆኑን የክፍለ ከተማው የትምህርት ጽህፈት ቤት ገልጿል።

ባለፉት ሁለት ቀናት በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አካባቢ በሚገኘው የካራ ማራ ትምህርት ቤት በመንግስት በኩል የተመቻቸው የቁርስና የምሳ ምገባ በአግባቡ አልተካሄደም።

የካራ ማራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የአደራጃጀት ርእስ መምህር አቶ ዮናስ ሽኩር እንደገለጹት፤ ምገባው የተቋረጠው ምግቡን እንዲያቀርቡ በማህበር የተደራጁ እናቶች የንግድ ፈቃድ የላቸውም።

በመሆኑም ከክፍያ አፈጻጸም ጋር ችግር በማጋጠሙ የተነሳ ምግብ አቅራቢ እናቶች የገንዘብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።

የፋይናንስ ስርዓቱ በሚፈቅደው መሰረት ክፍያ ለመፈጸም ዝግጁነት ቢኖርም የተደራጁት እናቶች የንግድ ፈቃድ የሌላቸው በመሆኑ እንቅፋት መፍጠሩን አቶ ዮናስ ተናግረዋል።

በዚህ የተነሳ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ምገባው ተቋርጧል።

በቀጣይ በከተማው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ምቹ የመማርና ማስተማር ድባብ ለመፍጠርና በዘላቂነት ምግባው እንዳይቋረጥ መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ የሴቶችና ህጻናትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ተስፋነሽ ጋሻ በበኩላቸው፤ ''ማህበራቱ ቀደም ብሎ በወረዳው ተደራጅተው የሚሰሩ ነበሩ'' ብለዋል።

''ተደራጅተው የሚሰሩት እናቶች የሚከፈላቸው የገንዘብ መጠን አነስተኛ በመሆኑ ታክስ መክፍል እንደማይችሉ አስታውቀውን ነበር'' ያሉት ኃላፊዋ ክፍያውን ለማስተካካል እንደሚሰራ ለተደራጁት እናቶች ተነግሯቸው ወደስራ እንዲገቡ ተደርጎ እንደነበር ገልጸዋል።

የንግድ ፈቃድ የማውጣት ሂደቱንም እንዲቀጥሉ ከመተማመን ላይ መደረሱን ተናግረው፤ ''በመሐል ትምህርት ቤቱ ክፍያውን መፈጸም ባለመቻሉ ለሁለት ቀን የምገባ መርሃግብሩ ተቋርጧል'' ብለዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ማህበራቱ ከትላንት ጀምሮ የንግድ ፍቃድ ለማውጣት እየሞከሩ ነው።

ሂደቱ ከተጠናቀቀና የገንዘብ ክፍያው ከተጠናቀቀ የምገባው መርሃ ግብር እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም