የተተከሉ ችግኞች በእንክብካቤ እጦት እየደረቁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተተከሉ ችግኞች በእንክብካቤ እጦት እየደረቁ ነው
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 22 ቀን 2012 ባለፈው ክረምት የተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ የመድረቅ አዝማሚያ እየተስተዋለባቸው ነው።
''በአረንጓዴ አሻራ'' ዘመቻ ባለፈው ክረምት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሚጠጉ አገር በቀልና የውጭ አገር ችግኞች መተከላቸው ይታወቃል።
የሃበሻና የፈረንጅ ፅድ፣ ባህር ዛፍና ግራር ከተተከሉ ችግኞች መካከል ናቸው።
በተለይም ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ግብ ተይዞ በዘመቻው ከታቀደው በላይ 350 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።
የግልና የመንግሥት ተቋማት፣ ባለስልጣናትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዘመቻው በመሳተፍ የተቀናጀ ርብርብ መደረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር በአንዳንድ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የተተከሉ ችግኞችን የተመለከተ ሲሆን እንክብካቤ ማድረግ ላይ ክፍተት መኖሩን ታዝቧል።
የውሃ እጥረት፣ የማረምና የመኮትኮት ችግር እንዳለ፤ እንዲሁም የተተከሉ ችግኞች ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ አለመደረጋቸውን መመልከት ተችሏል።
ይህ ደግሞ ችግኙ የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳይደርስ የሚያደርግ በመሆኑን መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚኖርባቸው አመላካች ነው።
አቶ ደርብ ይማም በአዲስ አባባ ዙሪያ ጌሾ ወንዝ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደን ጥበቃ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት መንግሥት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶባቸው የተተከሉት ችግኞች እንክብካቤ ባለማግኘታቸው እየደረቁ ነው።
''በርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተከሉትን ችግኝ ተከታትለው ይንከባከባሉ ተብሎ ነበር" ያሉት አቶ ደርብ አሁን ግን ዞር ብሎ እንኳን የሚያይ ጠፍቷል ይላሉ።
በአካባቢው ከፍተኛ የውኃ እጥረት መኖሩን የገለጹት አቶ ደርብ ''እኔ በግሌ ውኃ እያመጣሁ ነው እያጠጣሁ ያለሁት፤ ውኃ እየተወደደ በመሆኑ አቅም የለኝም ከዚህ በኋላ መንግሥት የሚጠበቅበትን ይወጣ'' ብለዋል።
ችግኞቹን ለማዳን መንግሥት በቦቴ ውኃ የሚያቀርብበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
በኮተቤ ጅፋራ በር አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ በቀለ ጉተማ በበኩላቸው ችግኞች የተተከሉባቸው ቦታዎች እንስሳት እየገቡ እያጠፉት እንደሆነና ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገ አለመሆኑን ተናግረዋል።
አቶ በቀለ ችግኞቹን መንግሥት በቋሚነት የሚንከባከብ ሰራተኛ ቀጥሮ ማሰራት አለበት ባይ ናቸው።
በኢትዮጵያ የደን ሽፋንን ለማወቅ በየሦስት ዓመቱ ጥናት የሚካሄድ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የደን ሽፋኗ 15 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።