ቀጥታ፡

የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ዲላ (ኢዜአ) ጥቅምት 22 ቀን 2012 የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ። በተለይ በዞኑ በሚመረቱ የምግብ የፍጆታ ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን ረዥም የግብይት ሰንሰለት በማስቀረት የዋጋ ንረቱን ማረጋጋት መቻሉንም ገልጿል፡፡ የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል  ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ጋሹ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ከንግዱ ማህበረሰብና ከሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት ጋር ተቀራርበው እየሰሩ ናቸው፡፡ ለእዚህም በአገር ደረጃ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ተከትሎ በዞኑ ያለውን ተመሳሳይ ገጽታ ለመቀየር ከሸማቾች፣ ከንግዱ ማህበረሰብና ከመንግስት አካላት የተወጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደሥራ መገባቱን ተናግረዋል። በፋብሪካ ምርቶችና ሸቀጦች ላይ እንዲሁም መንግስት ድጎማ በሚያደርግባቸው የፍጆታ ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ግብረ ኃይሉ ከሕብረተሰቡ ጋር በቅርበት እየሰራ ነው፡፡ በእዚህም ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 300 ነጋዴዎች ላይ የንግድ መደብራቸውን እስከማሸግ የደረሰ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱንም አቶ ወርቅነህ ተናግረዋል፡፡ መንግስት ድጎማ በሚያደርግባቸው የፍጆታ ምርቶች ላይ ያለአግባብ ዋጋ ጨምረው በተገኙ 6 የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራትም ፍቃዳቸው ተነጥቆ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ነው የገለጹት፡፡ "ቆጮን ጨምሮ በዞኑ የሚመረቱ አትክልትና ፍራፍሬዎች ላይ የሚስተዋሉ አላስፈላጊ ረዥም የግብይት ሰንሰለትን በመቀነስ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡ ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ጎን ለጎን የተጋነነ ጭማሪ በታየባቸው ሸቀጦች ላይ ማስተካከያ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ ዋጋ ለማረጋጋት በተከናወኑ ተግባራት የተፈለገውን ያህል ውጤት ባይገኝም የዋጋ ንረቱን በተወሰነ ደረጃ ማረጋጋት መቻሉን ነው የገለጹት፡፡ የጌዴኦ ዞን ሕብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረጀ ሾንጣ በበኩላቸው "የዋጋ ንረትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራትን የማጠናከሩ ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው " ብለዋል፡፡ የቁጥጥር ስራው በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ሲገጥመው ፈጥኖ ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን  እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። አስተያየት የሰጡ ሽማቾች በበኩላቸው በዞኑ ከቁጥጥር ጋር ተያይዞ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። በተለይ በፍጆ እቃዎች ላይ የሚታየውን የዋጋ ጭማሪ ለመቆጠጣር ብዙ መስራትን እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት፡፡ በህገ ወጥ ንግድንና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እየተሳተፉ ባሉ ግለሰቦች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ  እንዲወሰድም ሸማቾቹ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም