ጥቅምት 21/2012 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን በከተማዋ የጀመረውን የማህበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴ ጤናማ ማህበረሰብ ከመፍጠር ጎን ለጎን ለሁሉም የስፖርት አይነቶች ምንጭ እንዲሆን እየሰራሁ መሆኑን ገለጸ።
ይህንንም ለማሳካት ኮሚሽኑ የ2012 በጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በመገምገም በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል። የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርትን በማጠናከር ለሁሉም የስፖርት አይነቶች ተወዳዳሪዎች ምንጭ መሆን በሚችልበት ሁኔታ ምክክር ተደርጓል። በመድረኩም የተጀመረውን ማህበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴውን ለጤናማ ማህበረሰብ ከመፍጠሪያነት ባለፈ ለሁሉም የስፖርት አይነቶች ሁሉ ምንጭነት እንደሚጠቅም የከተማ አስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ዮናስ አረጋይ ገልጸዋል። አቶ ዮናስ እንደሚገልጹት፤ ይህንን የማህበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴውን ማህበረሰቡ ባህል እንዲያደርገው ይሰራል። ለስኬታማነቱም ኮሚሽኑ በዘርፉ የተሻለ እንቅስቃሴ ካላቸው 32 ከሚደርሱ የስፖርት አደረጃጀቶች ጋር ተፈራረሟል። ከእነዚህም ውስጥ የቴኳንዶ ክለብ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ደጋፊዎች፣ ከታዳጊዎች ስፖርት አደረጃጀቶችን ጨምሮ በከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን የሚመራው የትምህርት ቢሮ ይገኙበታል። ይህም እንቅስቃሴ እስከ ወረዳ በመግባት ለዘርፉ እድገትና የሁሉም ስፖርቶች ምንጭ እንዲሆን እንደሚሰራ አቶ ዮናስ ተናግረዋል። የማርሻል አርት ኮሚቴ ሰብሳቢና የማህበረሰብ ስፖርት አስተባባሪ ማስተር ዳዊት አብርሃም በበኩላቸው ይኸው የስፖርት እንቅስቃሴ እንደቅንጦት መታየቱ ስህተት መሆኑን ገልጸዋል። ''ለዘርፉ እድገትና ለአገራዊ ፋይዳው ሁሉም ሰው ለጤናማ ህይወትና ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታነት እንዲውል ግንዛቤ እንዲኖር ብዙ መሰራት አለበት'' ብለዋል። እስካሁን በተደረገው 5 ዙር የማህበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴም የተሳታፊው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።