ቀጥታ፡

የሀገሪቱን የቱሪዝም መስህቦች የማልማትና የማስተዋወቁ ተግባር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ሰኔ 12/2010 የቱሪዝም መስህቦች ለሀገር የሚሰጡትን ጠቀሜታ ለማሳደግ ለጎብኝዎች የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ማልማትና የማስተዋወቁ ተግባራት ሊተኮርባቸው እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር "በቱሪዝም  አገልግሎት ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት አካሄዷል፡፡ በውይይቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ሀገሪቷ ካላት የቱሪዝም ሀብት አንጻር  መጠቀም ያለባትን ያህል እንዳልተጠቀመች ይናገራሉ፡፡ ለዚህም የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ መሰራት ያለባቸው የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች አለማደግና የቱሪስት መስህቦቹን በሚፈለገው መጠን ያለማስተዋወቅ እንደ ዋነኞቹ ችግሮች ተነስተዋል፡፡ ስለሆነም ሀገሪቷ ከቱሪዝም መስህቦቿ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ለጎብኚዎች የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ማልማትና የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል፡፡ እንዲሁም የቱሪዝም መስህቦቹን በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የሀገሪቷ ኤምባሲዎች በኩል የማስተዋወቅ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ባለድርሻ አካላት ተናግረዋል፡፡ የትራቪል ኢትዮጵያ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳምራዊት ሞገስ የሀገሪቷ  የቱሪዝም መስህቦችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ  በዘርፉ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የሀገሪቷ ኤምባሲዎች የቱሪስት መስህቦቹን የማስተዋወቅ ስራን በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ደበላ በበኩላቸው በሀገሪቷ ለጎብኚዎች አገልግሎት የሚሰጡት ሆቴሎችና መሰል ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ የአገልግሎት ሰጪ ዘርፉን በእውቅትና በስልጠና መደገፍ እንደሚገባም አክለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሆቴሎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ዘመናዊ የአገልግሎት መስጫ መሳሪያዎችን ከውጪ እንዲያስገቡ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው በውይይት መድረኩ  የተነሱ ችግሮች በቀጣይ በእቅድ ውስጥ ተካተው ተገቢውን ምላሽ እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ ሀገሪቷም ከቱሪዝም ዘርፍ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንድታገኝም በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም