ለወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ስኬት የድርሻችንን እንወጣለን - የውጭና አገር በቀል የግል ድርጅቶች - ኢዜአ አማርኛ
ለወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ስኬት የድርሻችንን እንወጣለን - የውጭና አገር በቀል የግል ድርጅቶች
ጥቅምት 21/2012 የውጭና አገር በቀል የግሉ ዘርፍ ድርጅቶች ተወካዮች ለወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ ስኬት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናገሩ። 'አመርቂና ዘላቂ የስራ ዕድል ለሁሉም' በሚል መርህ ትናንት በአዲስ አበባ በተካሄደው ብሔራዊ የስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ጉባዔ በውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙ አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለፁ የድርጅት ተወካዮችም የኢትዮጵያ መንግስት ለቀጣዮቹ ዓመታት ለወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ እውን መሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል። የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ፕሮግራም ኃላፊ ፒተር ማተሩ ድርጅታቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ30 በላይ የአፍሪካ አገራትን በትምህርትና በፋይናንስ በመደገፍ ከድህነት ለማውጣት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። እስካሁንም ከሌሎች አገር በቀል ድርጅቶች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ብቻ በትምህርት ዘርፍ 62 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል። በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ደግሞ 10 ሚሊዮን ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግ 'ወጣቷ አፍሪካ ትሰራለች' የሚሰኝ አዲስ መርሃ ግብር የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል። ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ለመነሻ ያህል 300 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። መርሃ ግብሩ ትኩረቱን በአራት ዘርፎች እንደሚያደርግና የመንግስትን ስትራቴጂም የሚደግፍ መሆኑን ተናግረዋል። የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት አልጋ በአልጋ እንዳይደሉ ገልጸው፤ ስትራቴጂክ ዕቅዶችን ለመተግባር ከግሉና ከመንግስት ተቋማት ጋር በቅንጅት እንሰራለን ነው ያሉት። 'ሪኒው' የተሰኘን የግል ኩባንያ የወከሉት ላውራ ዴቨስ እንዳሉት ደግሞ ድርጅታቸው ካለፈው ሰባት ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ12 ኩባንያዎች ጋር እየሰራ ነው። በአብዛኛው መቀመጫቸውን አሜሪካ ካደረጉ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ጋር በመሆን ማኅበረሰባዊ ለውጥ በሚፈጥሩ የኢንቨስትመንት መስኮች በጨርቃጨርቅ፣ በማቀነባበር፣ በአገልግሎት፣ በኃይልና በሌሎችም መስኮች መሳተፉን ጠቅሰዋል። መቀመጫውን ለንደን ያደረገውና በጤናና በወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚሰራው የ'ቢግ ቢግ ፍላንትሮፒ' ፋውንዴሽን ተወካይ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ቀደም ሲል ለእናቶችና ህፃናት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል። በቀጣይ ደግሞ ከፌዴራልና ከክልል መንግስታት ጎን በመቆም በወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ድጋፍ እንደሚያደረግ አስታውቀዋል። በህጻናትና ወጣት ታዳጊዎች ትምህርታዊ ፕሮግራም ላይ የሚሰራው የአገር በቀሉ ድርጅት ዊዝ ኪድስ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብሩክታዊት ጥጋቡ ድርጅታቸው ዘለቄታዊ፣ የህብረተሰብን ችግር ያማከሉና ትርፋማ ስራዎችን የሚያበረታታ መሆኑን ይገልጻሉ። በመንግስት ይፋ የተደረገው የስራ ዕድል ፈጠራ የድርጊት መርሃ ግብር ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትና ድህንትን ለመቅረፍ እገዛ የሚያደርግ ነው ብለዋል። ተቋሙ ራዕይ ይንደፍ እንጂ አፈጻፀሙ ላይ የግሉ ዘርፍ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ገልጸው፤ በዚህ ረገድ ድርጅታቸው የታቀደው ግብ እንዲሳካ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ተናግረዋል። በአውሮጳዊያኑ አቆጣጠር ከ2020-2025 የወጣው የድርጊት መርሃ ግብር በዋናነት በስድስት ስትራቴጂዎች ላይ ተመርኩዞ ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል። የስራ ዕድል ፈጠራ ስትራቴጂዎቹ ስራ ፈጣሪ ማክሮ ፖሊሲዎችንና ፈጣን አገር በቀል የግል ዘርፍ መገንባት፣ ገበያ ተኮር የሰው ሃብት ልማትን ማሻሻል፣ አካታች የስራ ገበያ መፍጠር፣ ውጤታማና አምራች ስራ ፈጣሪ መስኮችን መፍጠር የሚሉ ናቸው። በትናንትናው ጉባዔ ከ450 በላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የክልል መስተዳደር ተወካዮች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮችና የውጭ አገር አጋር ድርጅት ተወካዮች ታድመዋል። በዕቅዱ መሰረት በ2012 ዓ.ም ለሶስት ሚሊዮን ወጣቶች፣ በቀጣይ ስድስት ዓመታት ደግሞ ለ14 ሚሊዮን ወጣቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ክፍለ ኢኮኖሚ የስራ ዕድል ይፈጠራል ነው የተባለው።