ሮቤ ወደ ሰላምና መረጋጋት እየተመለሰች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሮቤ ወደ ሰላምና መረጋጋት እየተመለሰች ነው
ጎባ ጥቅምት 21 / 2012 በባሌ ዞን የሮቤ ከተማ ወደ ሰላምና መረጋጋት መመለሷን የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ገለጹ። በከተማዋ ሰሞኑን ከተከሰተው ሁኔታ ጋር ተያይዞ 35 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ከንቲባው አቶ አደም ኡመር እንደገለጹት ከተማዋ ባለፈው ሳምንት ገጥሟት ከነበረው የጸጥታ ችግር ወጥታ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰዋል። የከተማዋን ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስከበር ጥረቱ እንደሚጠናከርም አስታውቀዋል። መንግሥት ብቻውን የከተማዋን ሰላም መጠበቅ አይችልም ያሉት አቶ አደም፣ ነዋሪዎች አጥፊዎችን በማጋለጥ፣የተረጋጋችና ለነዋሪዎቿ የተመቸች ከተማ ለመፍጠር የተያዘውን ጥረት እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡ በከተማዋ ሰሞኑን ከተከሰተው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ሕይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም የተጠረጠሩ 35 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማዋ አስተዳደር የፀጥታ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱረዛቅ መሐመድ ናቸው፡፡ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ለማቅረብ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ የከተማዋ ፖሊስና ዐቃቤያነ ሕግ የተካተቱበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከኅብረተሰቡ የሚቀርቡ ጥቆማዎች በማጣራት ለሕግ ለማቅረብ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ግብረ ኃይሉ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን ለማቅረብ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ትብብር እንዲያደርግ ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡