የጸጥታ ኃይሎቹ የተፈናቃዮችን ሰብል እየሰበሰቡ ነው

71
ጎንደር (ኢዜአ) ጥቅምት 21 ቀን 2012 በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በጸጥታ ማስከበር ሥራ የተሰማሩ የልዩ ኃይልና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በግጭት ከተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ የደረሰ የመኽር ሰብል እየሰበሰቡ መሆናቸውን የማእከላዊ ጎንደር ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ጌታሁን ለኢዜአ እንዳሉት የደረሱ ሰብሎችን እየሰበሰቡ ያሉት የ33ኛ ክፍለ ጦር የመከላከለያ ሠራዊትና የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ናቸው፡፡ የጸጥታ ኃይሎቹ በወረዳው አምቦ በር በተባለ ቀበሌ ከትላንት ጀምሮ እያከናወኑ ባለው የሰብል ስብሰባ ሥራ ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን እያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የደረሱ የጤፍ ሰብሎችን በማጨድና በመከመር ከጉዳት ለመታደግ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተፈናቃዮች ተረጋግተው እንዲኖሩ ለማድረግ አስተዋጻ እንዳለው ገልጸዋል። በወረዳው አራት ቀበሌዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው በጊዚያዊ መጠለያ የነበሩ አባውራና ቤተሰቦቻቸው በአካባቢው ሰላም በመስፈኑ ከተያዘው ሳምንት ጀምሮ ወደ መኖሪያ ቄያቸው መመለስ መጀመራቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም