የኢህአዴግ ውህደት ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን ሆነው ጠንካራ ኢትዮጵያ የሚገነባበት እንደሆነ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢህአዴግ ውህደት ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን ሆነው ጠንካራ ኢትዮጵያ የሚገነባበት እንደሆነ ተገለጸ
ጥቅምት 21/2012 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ውህደት ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን ሆነው ጠንካራ ኢትዮጵያ የሚገነባበት እንደሆነና ለፖለቲካ ንግድ የማይመች መሆኑ ተገለጸ። ውህደቱ አሃዳዊ ስርዓት ለመመስረት የሚደረግ ጥረት እንደሆነ በመግለጽ ግጭትን ከሚሰብኩ አካላት መጠንቀቅ እንደሚገባ መንግስት አሳሰበ። የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑም ተገልጿል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ትናንት ማምሻው በሰጡት መግለጫ የኢህአዴግ ውህደትን በተመለከተ ሃሳብ አንስተዋል። አቶ ንጉሱ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ለበርካታ ዓመታት ፓርቲና አገር አንድ እንደሆኑ ተደርጎ በመሰበኩ ምክንያት ዜጎች የኢህአዴግ ውህደት ጉዳይ እያሳሰባቸው ይገኛል። ይህን ጉዳይ እንደምቹ ሁኔታ በመውሰድ ውህደቱ የአንድ ወገን የበላይነት ለማምጣት የሚደረግ ጥረት በማስመሰል ውዥምብር የሚፈጥሩ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል። የለውጡ አመራሮች የአንድ ወገን የበላይነት እንዲያከትም አምርረው መታገላቸውንም አስታውሰዋል። የአንድ ወገን የበላይነት እንዲመጣ የሚፈልግ አካል ቢኖር እንኳ ይህን መሸከም የሚችል ትከሻ አለመኖሩን ገልጸዋል። በሌላ መልኩ ውህደቱን የፌደራሊዝም ሰርዓቱን በማፍረስ አሃዳዊ ሰርዓት ለመገንባት የሚደረግ ጉዞ በማስመሰል ግጭት የሚሰብኩ አካላት እንዳሉም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል። ነገር ግን ኢህአዴግ የፌደራሊዝም ስርዓቱን መናድ ማለት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ማንነት መሸርሸር መሆኑን እንደሚገነዘብ ገልጸዋል። የውህደቱ ዓላማ አንዱ አጋር ተብሎ ኢህአዴግ የወሰነውን እንዲፈጽም ሳይገደድ ሁሉም ድርጅቶች እኩል የሚሳተፉበት ፓርቲ መመስረት እንደሆነም አብራርተዋል። አሃዳዊነትን ለመመለስ እየተሰራ እንደሆነ የሚሳለው ስዕል የተሳሳተ መሆኑን የገለጹት አቶ ንጉሱ፤ አሃዳዊነትን ኢትዮጵያ ልትሸከመው የማትችልውና ትውልድ የማይቀበለው ተግባር መሆኑን አስረድተዋል። ኢህአዴግም የማይቀበለውና ፌዴራላዊ ስርዓቱን ጠብቆ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። የፌደራል ስርዓቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነታቸውን ሳይለቁ በአንድነት ጠንካራ አገር ለመገንባት ያስቻለ ስርዓት መሆኑንም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል። በመሆኑም "የፓርቲ ውህደቱና የለውጡ ቁልፍ አጀንዳ አሃዳዊነትን መመለስ ነው" እያሉ የሃሰት አጀንዳ በሚፈጥሩ ወገኖች መደናገር እንደማይገባ አሳስበዋል።