ቀጥታ፡

የቀይ ቦሎቄና አረንጓዴ ማሾ ግብይት ተግባራዊ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 21/2012 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 7 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 131 ሺህ ቶን ምርቶችን ማገበያየቱን አስታውቋል። ይህ የግብይት አፈጻጸም የዕቅዱን መጠን  140 በመቶ እንዲሁም በዋጋ 145 በመቶ ያሳካ ሲሆን አፈጻጸሙ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን የ86 በመቶ እንዲሁም በዋጋ የ70 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የቀይ ቦሎቄና አረንጓዴ ማሾ ግብይት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ብቻ እንዲከናወን በመደረጉ ባለፉት ወራት 7 ሺ 065 ኩንታል አረንጓዴ ማሾ ለግብይት ቀርቦ በ216 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር መገበያየቱን ምርት ገበያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ ያሳያል፡፡ ቀይ ቦሎቄና አረንጓዴ ማሾ ግብይታቸው አስገዳጅ ሆኖ በምርት ገበያው ብቻ እንዲገበያዩ የተደረገው የወጪ ንግዱን ለማሳደግና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ታስቦ  መሆኑም ተገልጿል። በምርት ግብይቱ ቡና 57 በመቶ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሲሆን በተለይ አኩሪ አተር በታህሳስ 2011 ዓ.ም ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ ግብይቱ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡፡ በሩብ ዓመት 79 ሺ 202 ቶን ቡና በ5 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር፣ 25 ሺ 882 ቶን አኩሪ አተር በ396 ሚሊየን ብር፣ 14 ሺ 926 ቶን ሰሊጥ በ835 ሚሊየን ብር፣ 4 ሺ 009 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ 83 ሚሊየን ብር ተገበያይተዋል ፡፡ ምርት ገበያው በከፈታቸው የክልል የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከላት አማካይነት ባለፉት ሦስት ወራት በሀዋሳ የግብይት ማዕከል 25 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው 314 ሜትሪክ ቶን ቡና፤ በሁመራ ማዕከል 26 ሚሊየን ብር ግምት ያለው 443 ሜትሪክ ቶን ሰሊጥ ማገበያየት ተችሏል፡፡ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በምርት ገበያው መጋዘኖች በማከማቸት ከባንኮች ብድር የሚያገኙበት አሰራር ለመዘርጋት ጥናት ተደርጎ የተጠናቀቀ ሲሆን በ2012 በጀት ዓመት በሙከራ ደረጃ በበቆሎ ምርት በቡሬና በነቀምቴ የምርት ገበያው ቅርንጫፎች ለመተግበር የዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ አርሶ አደሩ፣ አቅራቢዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የግብይት መረጃ እንዲያገኙ የሚረዱ 66 የገበያ መረጃ ማሰራጫ ኪዮስኮች  በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች መተከላቸውን የምረት ገበያው መግለጫ ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም