ባዮጋዝ አማራጭና ጤንነታችንን የምንጠበቅበት ኃይል ነው-የደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ባዮጋዝ አማራጭና ጤንነታችንን የምንጠበቅበት ኃይል ነው-የደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሮች
ደሴ ጥቅምት 20 ቀን 2012 ባዮጋዝ አማራጭና ጤንነታቸውን የሚጠበቁበት ኃይል ሆኖ እንዳገኙት የደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።
የአማራ ክልል የባዮጋዝ ፌስቲቫል በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ እየተካሄደ ነው፡፡
የዞኑ አንዳንድ አርሶ አደሮች እንደተናገሩት ባዮ ጋዝ ለዘመናት ይገጥሟቸውን ከነበሩት ችግሮች ያላቀቀና ጤንነታቸውን የሚጠብቁበት የኃይል ምንጭ ሆኖላቸዋል።
በወረኢሉ ወረዳ የ07 ቀበሌ ነዋሪዋ አርሶ አደር አሰገደች አበጋዝ እንደገለጹት ቀደም ሲል የምግብ ማብሰያ ማገዶ እንጨት ፍለጋ ረጅም ርቀት ይጓዙ ነበር።
ከደን የሚያመጡትን እንጨት ሲጠቀሙ ደግሞ ጢሱ በጤናቸው ላይ እክል ይፈጥር እንደነበር ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት በአካባቢያቸው የተገነባው ባዮ ጋዝ ችግራቸውን እንዳቃለላቸው ተናግረዋል፡፡
ባዮ ጋዝ አራት ልጆቻቸው ያለ ስጋት የሚያነቡበት ብርሃን እንደሰጣቸው፣ በጢስ ከመታፈን እንዳዳናቸውና ተረፈ ምርቱን በማዳበሪያነት ለመጠቀም ችያለሁ ብለዋል።
አርሶ አደር ሻምበል አወል በበኩላቸው ካለፈው ዓመት ጀምሮ ባስገነቡት ባዮ ጋዝ ከአራት ከብቶቻቸው የሚወጣውን እበት በመጠቀም መብራትና ማብሰያዎችን መጠቀም ጀምረዋል።
ምጣድ ለማሰራትም ዝግጅት አድርጌያለሁ ብለዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ውሃ ፣መስኖና ኢነርጂ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ሽመልስ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ዓመታት በተገነቡ ባዮ ጋዞች ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ተጠቅመዋል።
አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂውን ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎቱ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው በበኩላቸው አርሶ አደሩ የባዮ ጋዝ ተጠቃሚ በመሆኑ የደን ጭፍጨፋ መቀነሱን ገልጸዋል።
በክልሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተገነቡት ከ9ሺህ 700 በላይ ባዮጋዝ በመገንባት ከ40 ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
በዚህም እናቶች በጢስ ከመታፈን ከመዳናቸው በላይ ማገዶ ፍለጋ ያጠፉት የነበረውን ጊዜና ጉልበት ማዳናቸውን ኃላፊው አመልክተዋል።
ተማሪዎች ከኩራዝ ተላቀው በመብራት በማጥናታቸው የትምህርትን ጥራት መሻሻል እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል።
ቢሮው በያዝነው ዓመትም ከሦስት ሺህ በላይ ባዮ ጋዝ ለመገንባት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በፌስቲቫሉ ከክልልና ከዞን የተውጣጡ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።