ቀጥታ፡

ኢኒስቲትዩቱ የተፈጥሮና የብዝሀ ህይወት ሀብቶችን ጠብቆ ለማቆየት እየሰራ ነው

መቱ (ኢዜአ) ጥቅምት 20 ቀን 2012 የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢኒስቲትዩት በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢ የሚገኙትን የተፈጥሮና የብዝሀ ህይወት ሀብቶችን ጠብቆ ለማቆየት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በኢኒስቲትዩቱ የመቱ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ናኦል ባዩ ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከሉ ይህን ሥራ እያከናወነ ያለው ከህብረተሰቡና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመተባበር ነው።

“በእዚህም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተለያዩ አገር በቀል የደን ዝርያዎችን በማባዛት ላይ ይገኛል” ብለዋል።

በኢሉአባቦር፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ጅማ እና ከፋ ዞኖች አራት የዘረ መል ባንክ በማቋቋም የእህል፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ የደን እና ቡና ዝርያዎችን እያሰባሰበ መሆኑንም ነው አቶ ናኦል የገለጹት።

ከእዚህ በተጨማሪ ማዕከሉ በምስራቅ ወለጋ ሌቃ ዱለቻ እና አርጆ ጉደቱ አካባቢዎች 98 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ አተር፣ ባቄላና ገብስን ጨምሮ ዘጠኝ አይነት ምርጥ የእህል ዝርያዎችን የማባዛት ሥራ እያከናወነ ይገኛል።

በከፋ ዞን ዴቻ እና ጨና ወረዳዎችም ከ150 በላይ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘረመል የማባዛት ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

“በአካባቢው በዩኔስኮ የተመዘገበውን የያዮ ተፈጥሮ ደን እንዲሁም የሸካ እና ማጃንግ ጥቅጥቅ ደንን ለመጠበቅና ለመንከባከብ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ከመቱ ፣ ወለጋ፣ ቦንጋ እና ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ማዕከሉ በትብብር እየተሰራ ነው” ሲሉም አቶ ናኦል አመልክተዋል።

ኢኒስቲትዩቱ በያዮ የተፈጥሮ ደን አካባቢ በአራት ሄክታር መሬት ላይ የደን እና ቡና ዘረመል ባንክ በማቋቋም ዝርያን የማባዛት እና የማቆየት ሥራ እየሰራ ይገኛል።

በዚህ ዓመትም በደኖቹ አካባቢ ከ125ሺህ በላይ የአገር በቀል ደን ዝርያዎችን ለመትከል መታቀዱን ነው የጠቆሙት።

በኢሉአባቦር ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ሽፋ ጣሂር እንዳሉት በዞኑ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅ ማዕከሉ እያከናወነ ያለው ተግባር በዘርፉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችል ነው።

ጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ደኑን ለመጠበቅና በውስጡ የጫካ ቡና እና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች በስፋት እንዲለሙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል::

በያዮ ወረዳ ጌሪ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ተሾመ ቀነዓ እንዳሉት የአካባቢያቸውን ደን በመጠበቅና የጫካ ቡና በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማዕከሉ ከግብርና ፅህፈት ቤት ጋር በመሆን ግንዛቤያቸውን የማሳደግ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል::

በአሁኑ ወቅትም በሁለት ሄክታር መሬት ላይ የተሰጣቸውን የጫካ ቡና ከማልማት ባለፈ በንብ ማነብ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

የኢሉአባቦር ዞን ከ167 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍነውና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት ፣ የባህልና የሳይንስ ማዕከል (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ያዮ ተፈጥሮ ደን የሚገኝበት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም