ለሶስተኛ ድግሪ ትምህርት ጥራትና ብቃት ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ለሶስተኛ ድግሪ ትምህርት ጥራትና ብቃት ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ተባለ
ጅማ ጥቅምት 20/2012 በኢትዮጵያ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚሰጠው የሶስተኛ ድግሪ (ዶክትሬት) ትምህርት ጥራትና ብቃት ይጠናከር ዘንድ ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲል የጅማ ዩኒቨርስቲ ገለፀ።
በአሁኑ ወቅት በተለይ የአገሪቱ አንጋፋ ዩኒቨርስቲዎች በተለያዩ የእውቀት መስኮች የሶስተኛ ድግሪ (ዶክትሬት) ትምህርት በመስጠት ላይ ናቸው።
ሆኖም የሚሰጠው ትምህርት ከጥራትና ብቃት ጋር በተያያዘ ችግሮች የሚስተዋሉበት መሆኑ ይነገራል።
የጅማ ዩንቨርሲቲ በዚህ ረገድ የሚስተዋሉትን ተግዳሮቶች ለመመከትና ጥራቱን የጠበቀ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ለዚህም ይረዳው ዘንድ ከኖርዌው የኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የትምህርት ጥራት ፕሮጀክት በመንደፍ ወደተግባር መግባቱን ዩኒቨርስቲው ገልጿል።
በፕሮጀክቱ ላይ የመከረ አውደ ጥናት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የኦስሎ ዩንቨርሲቲን ጨምሮ ከ33 የኢትዮጵያ ዩንቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራንና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።
በዚሁ ወቅት በጅማ ዩንቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አዱላ በቀለ እንደገለጹት የተማሪው የአቅም ውስንነት፣ ለፕሮግራሙ የሚመደበው በጀት ማነስና የትምህርት መሰረተ ልማት አለመሟላት በሶስተኛ ድግሪ ትምህርት ላይ እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች መካከል ናቸው።
የዶክትሬት ትምህርት ትኩረት ጥናትና ምርምር ሆኖ ሳለ አስካሁን ባለው አሰራር ግን ተማሪዎች ወደጥናትና ምርምር ተግባር የሚሰማሩት ትምህርቱን ከጀመሩ ሁለት ዓመታት በኋላ ነው፤ ይህም በደረጃው የሚሰጠው ትምህርት ጥራት ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን ዶክተር አዱላ ይናገራሉ።
በሌሎች ዓለም አቀፍ የትምህርት ተቋማት ያለው አሰራር በዚህ ደረጃ የሚሰጠው ስልጠና ሙሉ ትኩረቱ ጥናትና ምርምር መሆኑም ተመልክቷ።
በመሆኑም ጥናትና ምርምሩ ከመጀመሪያው ዓመት ጀምሮ እስከማብቂያው ድረስ ያለሟቋረጥ መከናወን እንዳለበት ነው ዶክተር አዱላ ያሳሰቡት።
ሌሎች የአለም አቀፍ ዩንቨርሲቲዎች ውጤታማነት ለመከተል የተጀመረው እንቅስቃሴ ሊበረታታ ይገባል፤ ሆኖም ይህ ተመክሮ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር መቆራኘት አለበት ያሉት ደግሞ የአዲስ ኮንቲኔንታል የጤና አጠባበቅ ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የማነ ብርሃን ናቸው።
በኖርዌይ ዩንቨርሲቲ የጤና ዘርፍ አመራር ፕሮፌሰር ጄኔት ማግነስ፣ በሶስተኛ ድግሪ የትምህርት ዘርፍ ጥራትን ለመጠበቅ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብትና ልማት ለማሳደግ የሚያግዝ ጥራቱን የጠበቀ የሰው ኃይል ማፍራት ያዳግታል።
ጅማ ዩንቨርሲቲ እንደ ኖርዌይ ካሉ አለም አቀፍ ዩነቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ያለውን አሰራር ለማጎልበት እየሄደበት ያለውን መንገድ ሌሎችም ተመሳሳይ ዩኒቨርስቲዎች ሊከተሉት ይገባል ሲሉ ገለጸዋል ፕሮፌሰሯ።
በአሁኑ ወቅት የጅማ ዩንቨርሲቲ ብቻ ከ300 በላይ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል።