የአንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያስከትል የመከላከል ሥራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያስከትል የመከላከል ሥራ እየተሰራ ነው
ጥቅምት 20/2012 ድንበር ተሻጋሪ የበረሃ አንበጣ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያስከትል የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት /FAO/ በቅርቡ ባወጣው ማስጠንቀቂያ ሕንድ፣ ፓኪስታንና ኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣ መንጋ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁሞ ነበር። በዚህም በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በአፋር ክልልና በድሬዳዋ አቅራቢያ የአንበጣ መንጋ መስተዋሉንና እንቁላሎቹም አድገው እየጎለመሱ መሆኑን አስታውቆ ነበር። ይሄን ጉዳይ በሚመለከት ኢዜአ በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሰላቶን አነጋግሯል። ኃላፊው በሰጡት ምላሽም ድንበር ተሻጋሪ የበረሃ አንበጣ መንጋ ካለፈው ሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ከየመንና ሶማሊ ላንድ ወደ ኢትዮጵያ መዛመቱን ተናግረዋል። በአፋር ክልል አድርጎ የገባው የአንበጣ መንጋው በአማራና ትግራይ አዋሳኝ ወረዳዎች የተዘመተ መሆኑን ገልፀው፤ በሱማሌ ክልል የገባው ደግሞ በኦሮሚያና ድሬዳዋ አካባቢዎች ላይ መዛመቱን አስረድተዋል። አንበጣው ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት ከጎሮቤት አገራትና በዘርፉ ከሚሰሩ አካላት ጋር በነበረው የመረጃ ልውውጥ ለመከላከል በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። ለዚህም ለመከላከል የሚያስፈልገው የበጀት ድጋፍ ፣ የፀረ ተባይ መርጫ መሳሪያ፣ የባለሙያ እንዲሁም አውሮፕላንን ጨምሮ ተሽከርካሪ መኪና የአንበጣ መንጋው ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች በማስጠጋት መንጋው እንቁላል እንዳይጥልና ስርጭቱን ለመቀነስ ሙከራ መደረጉን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ሊደረስባቸው ባልተቻሉ አካባቢዎች ላይ ከዚህ ቀደም የተራረፉ የአንበጣ መንጋዎች የጣሉት እንቁላል ከመስከረም ጀምሮ በአፋር ክልል አንዳንድ ወረዳዎች ላይ መፈልፈላቸውን ገልፀዋል። ይሄን ለመከላከልም የፌደራል፣ የክልልና የዞን ባለሙያዎች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የአንበጣ መንጋው እንቁላል ያለባቸውንና የሌለባቸውን አካባቢዎች በመለየት ለመከላከል መቻሉን ተናግረዋል። አሁን ላይ የታየው የአንበጣ መንጋም ከመከላከል ስራው የተረፉ የተወሰኑ የአንበጣ መንጋዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በአፋር፣ በአማራና በትግራይ አካባቢዎች ላይ አሁን የተከሰተውን የአንበጣ መንጋም ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመከላከልም መንግስት ከህብረተቡ ጋር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል። የአንበጣው መንጋ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ የፌደራልና የክልል ባለሙያዎች የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው ህብረተሰቡም በባህላዊ መንገድ ለመከላከልና አንበጣዎቹን ለማባረር እየተረባረበ መሆኑን ተናግረዋል። የአንበጣ መንጋው በስፋት ወዳለባቸው በተመረጡ አካባቢዎች ላይ ደግሞ በአውሮፕላን የታገዘ ፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም ከድሬዳዋ፣ መቀሌና ኮምበልቻ አየር ማረፊያዎች አውሮፕላኖች እየተመላለሱ የርጭት ስራውን እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል። ድንበር ተሻጋሪ የበረሃ አንበጣ መንጋው እስካሁን ድረስ "በተፈጥሮ ሀብትና ሰብል ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አድርሷል ብሎ መናገር እንደሚከብድ" የተናገሩት ኃላፊው፤ ምናልባት የተንጠባጠበ ጉዳት አድርሶም ከሆነ ከመከላከል በኋላ የጉዳት መጠን በሚሰሩ ባለሙያዎች የሚታይ እንደሚሆን ነው የገለፁት። ነገር ግን ህብረተሰቡ እንደሚለው በምርት ላይ ያደረሰው ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖም ሆነ ጉዳት እስካሁን እንደሌለም አጽኖኦት ሰጥተውታል ዳይሬክተሩ።