በተቋማቱ የሚሰጡ ስልጠናዎችና ምርምሮች ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ጋር መሳለጥ ይገባቸዋል-ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
በተቋማቱ የሚሰጡ ስልጠናዎችና ምርምሮች ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ጋር መሳለጥ ይገባቸዋል-ሚኒስቴሩ

ጅማ ጥቅምት 20/ 2012 በከፍተኛ ትምህርት የሚሰጡ ስልጠናዎችና ምርምሮች ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ጋር መሳለጥ እንደሚገባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ ሚኒስቴሩ በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ''አይ ሲ ቲ ለከፍተኛ ዩኒቨርሲቲ ስልጠናና ተቋማት ሁለንተናዊ ልህቀት!'' በሚል መሪ ቃል የሁለት ቀናት ጉባዔ በጅማ ተጀምሯል፡፡ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር እሸቱ ከበደ እንዳመለከቱት ተቋማቱ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን ለሥራቸው ግብዓት በማድረግ ሥራቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል። ቴክኖሎጂው ከትምህርት መሳሪያነት አልፎ፤የትምህርት ቋንቋ ወደ መሆን እየተሸጋገረ መሆኑን አመልክተው፣ተቋማቱ ቴክኖሎጂውን ለማስፋፋት ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል። በቴክኖሎጂው በፍጥነት እየተለወጠች ባለችው ዓለም ብንችል ቀዳሚ፤ ካልቻልን ተከታይ ሆነን እንዲያደርገን መሥራት ይኖርብናል ብለዋል። በአዲሱ የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ቴክኖሎጂው ከደረሰበት ደረጃ ጋር የሚዛመድ ዕውቀትና ክህሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በሚሰጠው አገልግሎት ቴክኖሎጂውን የተሳሰረና የተሳለጠ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቴር ዶክተር ብርኩ ከተማ ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂው ራሱን ማደራጀቱን ገልጸው፣በአገሪቱ ከሚገኙ 15 ዩኒቨርሲዎች ጋር በኔትዎርክ፣በመተግበሪያና በስልጠና ዙሪያ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ታደሰ ጉባዔው በዘርፉ ያሉትን ችግሮች የሚለዩበት፣የሚፈቱበትና ልምድ የሚለዋወጡበት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ጉባዔው የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ መፍጠሩን ዩተናገሩት ፈግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶኃይለማሪያም ቀሬ ናቸው፡፡