ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና መካናይዜሽን እንዲሟላላቸው በደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና መካናይዜሽን እንዲሟላላቸው በደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ጠየቁ
ደሴ (ኢዜአ) ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም--- በደቡብ ወሎ ዞን የስንዴ ምርታማነታቸውን ለማሳደግና የምርት ብክነትን ለመቀነስ የግብርና መካናይዜሽን አቅርቦት ሊሟላልን ይገባል ሲሉ አርሶ አደሮች ጠየቁ። በዞኑ ጃማና ወረኢሉ ወረዳ የለማው የስንዴ ሰብል ትናንት በአመራር አካላት ተጎብኝቷል። በጃማ ወረዳ የቀበሌ 11 ነዋሪ አርሶ አደር አህመድ ሰይድ እንደገለጹት አካባቢው ለስንዴ ልማት ምቹ በመሆኑ በየዓመቱ ከአንድ ሄክታር በላይ መሬት ስንዴ በማልማት ከ45 ኩንታል በላይ ምርት ያገኛሉ። ይሁን እንጂ የማረሻ፣ መውቂያና ማጨጃ ማሽን በአካባቢው ባለመኖሩ በልፋታቸው ልክ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። "ምርት ስንሰበስብና ስንወቃ የምርት ብክነት እየገጠመን ነው" ያሉት አርሶ አደሩ መንግስት የግብርና መካናይዜሽን ተጠቃሚ እንዲያደርጋቸው ጠይቀዋል። በወረኢሉ ወረዳ ቀበሌ 9 ነዋሪ አርሶ አደር አራጌ ሙህዬ በበኩላቸው በባለሙያ ምክር ታግዘው በኩታ ገጠም በማልማታቸው ቀደም ሲል ከ25 ኩንታል በታች ያገኙበት ከነበረው አንድ ሄክታር መሬት በአሁኑ ወቅት ከ36 ኩንታል በላይ እያመረቱበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "የግብርና መካናይዜሽን ተጠቃሚ ብንሆን ምርታችንን የበለጠ ማሳደግ እንችል ነበር" ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሟቸው ትራክተሮች ድካማቸውን እንዳቀለሉላቸው ገልጸው ለምርት መሰብሰቢያና መውቂያ የሚሆኑ ማሽኖች እንዲቀርቡላቸው ጠይቀዋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ በበኩላቸው የአካባቢውን ስንዴ የማምረት አቅም ባገናዘበ መልኩ በኩታ ገጠም እንዲለማ መደረጉን ተናግረዋል። በየዓመቱ በዞኑ አጠቃላይ ከሚለማው መሬት ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው በስንዴ ሰብል እንደሚሸፈንም ነው የገለጹት ከሦስት ዓመታት በፊት ከ100 ሺህ ሄክታር መሬት በታች ስንዴ ይለማ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው በየዓመቱ የማምረት አቅምን በማሳደግ ዘንድሮ ከ146 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ መልማቱን ተናግረዋል፡፡ "ከ200 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍና የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከለማው የስንዴ ሰብልም ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርትም ይጠበቃል" ብለዋል፡፡ አርሶ አደሮች የግብርና መካናይዜሽን ተጠቃሚ ቢሆኑ ይብልጥ ምርታማ መሆን እንደሚችሉ በጥናት መረጋገጡን አቶ ታደሰ ተናግረዋል። ይሁንና እስከዛሬ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው በየዓመቱ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ምርት ለብክነት ተዳርጓል። አቶ ታደሰ እንዳሉት ባለፈው ዓመት 10 ዘመናዊ የትራክተር ማረሻዎችን በዩኒየኖች በኩል ከውጭ አገር በማስገባት ከ150 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሷል። ውጤቱ አመርቂ በመሆኑ የአርሶ አደሩ ፍላጎት ጨምሯል፣ ዘንድሮም ከሦስት በላይ ማጨጃና መውቂያ ማሽን ለማስገባት ከክልሉ መንግስት ጋር እየተሰራ መሆኑን ነው ኃላፊው የገለጹት። "በተለይ በመካናይዜሽን ለመስራት ምቹ የሆኑ ሰባት ወረዳዎች በዚህ ዓመት አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ከወዲሁ እየተሰራ ነው" ሲሉም ገልጸ። በጉብኝቱ ላይ በየደረጃ የሚገኙ የአማራ ክልል አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።