መደመር የህዝቦችን የአብሮነት እሴቶች በማጎልበት ሀገሪቱን ወደ ተሻለ እድገት ያሸጋግራል ... የጋምቤላ ክልል አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
መደመር የህዝቦችን የአብሮነት እሴቶች በማጎልበት ሀገሪቱን ወደ ተሻለ እድገት ያሸጋግራል ... የጋምቤላ ክልል አመራሮች
ጥቅምት 19/2012 መደመር የህዝቦችን የአንድነትና የአብሮነት እሴቶች በማጎልበት ሀገሪቱን ወደ ተሻለ እድገትና ብልጽግና ለማሸጋገር የሚያስችል ፍልስፍና መሆኑን በጋምቤላ ክልል ኢዜአ ያነጋገራቸው ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ። አመራሮቹ እንዳሉት ኢህአዴግ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት የቀየሰው አቅጣጫ አጋር ድርጀቶች በሀገሪቱ ጉዳይ እኩል የመወሰን መብት እንዲኖራቸው ሲያቀረቡት ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥም ነው። በመደመር ፍልስፍና ዙሪያ ስልጠና መውሰዳቸውን አመልክተው ፍልስፍናው ቀደም ሲል የነበሩ አሀዳዊነትና ተናጠላዊ አስተሳቦችን በማስቀረት ሀገራዊ አንድነት እንደሚጠናከር መገንዘባቸውን ተናግረዋል። ከአመራሮች መካከል አቶ ሰናይ አኩዎር በሰጡት አስተያየት "የመደመር ጽንሰ ሃሳብ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሄደባቸውን የተሰሳተ የጉዞ መስመር በማስተካከል ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ማስረከብ ያለመ ነው "ብለዋል። ህገ-መንግስቱና የፌደራለዝም ስርዓቱ የኢትዮጵያ ህዝቦችን እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ክፍተት ባይኖርበትም በአተገባበር ችግር ምክንያት ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል። "ለዚህም ዋነኛው ማሳያ ጋምቤላን ጨምሮ አጋር ድርጅቶች ተብለው የሚጠሩት ክልሎች በሀገሪቱ ጉዳዮች እኩል የመወሰን መብት ተነፍጓቸው መቆየቱ ነው "ብለዋል። ለውጡን ተከትሎ ግንባሩ አጋር ድርጅቶችን አካቶ አንድ ፓርቲ ለመመስረት የቀየሰው አቅጣጫ አጋር ድርጅቶች እኩል የመወሰን መብት እንዲኖራቸው ሲያቀርቡት ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። "የመደመር ፍልስፍና በአብዮታዊ ዴሞክራሲና ሌሎች ቀደምት ስርዓቶች ሲከተሉት ከነበሩት የተሻለና በሀገሪቱ የህዝቦች የተጠናከር አንድነት ለመፍጠር የሚያስችል እሳቤ ነው "ያሉት ደግሞ ሌላው አመራር አቶ ኡቶው እኮት ናቸው። በተለይም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ባሳለፈው የጉዞ መስመር ብሔር ብሔረሰቦች እራሳቸውን እንዲያቁ ብቻ በመስራቱ የአብሮነት እሴቶች ተሸርሽረው በግለኝነት አስተሳቦች በህዝቦች መካከል ልዩነቶች እንዲፈጠሩ ማድረጉን አስረድተዋል ። እራስን በራስ የማስተዳደር መብት በህገ - መንግስቱ የተረጋገጠ ቢሆንም አዳጊ በሚባሉ ክልሎች አስተዳደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ከማዕከላዊ መንግስቱ በሚላኩ አማካሪዎች ግፊት ሲከናወን መቆቱንም አስታውሰዋል። በዚህም ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ የክልሉ በርካታ መሬት ባለሃበቶች ናቸው በተባሉ አካላት ተወስዶ ለአካባቢው ማህበረሰብ በማይጠቅም መልኩ በመሬቱ ከልማት ባንክ ብድር ወስዳው የጠፉበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል። ሌላው አመራር አቶ ሙሴ ጋጂዬት " የመደመር እሳቤ አካባቢያዊ አስተሳሰቦችን በማስቀረት ለሀገራዊ አንድነት ግንባታ የጎላ ፋይዳ ያለው ጽንሰ ሃሳብ ነው" ብለዋል። በተለይም የመደመር ፍልስና ቀደም ሲል ተናጥላዊ የነበሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚዊና ማህበራዊ አቅሞችን በመጠመር ሀገሪቱን ወደ ተሻለ እድገትና ብልጽግና የማሻገር እሳቤን የሰነቀ መሆኑን ጠቁመዋል። ባለፉት 27 ዓመት በነበረው የግንባሩ ጉዞ አጋር ድርጅቶች በሀገራዊ ጉዳይ የመወሰን መብት መነፈጋቸው ስህተት እንደነበረ ጠቁመው ውህደቱ ይህን ችግር እንደሚፈታ ተናግረዋል። "መደመር በተለይም ታደጊ ተብለው ሲፈረጁ የነበሩትን ክልሎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እኩል የመወሰን መብትን ያረጋገጣል" ያሉት ደግሞ አቶ ቲቶ ሃዋሪያት ናቸው። ከአሁን በፊት የነበረው ሂደት በህዝቦች መካከል የመበላለጥ እሳቤ እንደነበረውም ጠቁመዋል።