ቀጥታ፡

በከተሞች እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር በአግባቡ ለመምራት የትብብር አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ  ጥቅምት  19/2012 በከተሞች እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር በአግባቡ ለመምራትና ፍላጎታቸውን ለማሟላት የትብብር አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ ተናገሩ። ሚኒስቴሩ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የከተማ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የከተሞች የትብብር አሰራር ስርዓትን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። በኢትዮጵያ በከተማ የሚኖረው የህዝብ ቁጥር ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተለይም ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ ነው ። ነገር ግን መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የከተማ የህዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በፈጣን ሁኔታ በማደግ ላይ ነው። ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ እንዳሉት፤ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር በአግባቡ ለመምራትና የከተሞችን እድገት ፈጣንና ቀጣይ ለማድረግ የትብብር አሰራርን መዘርጋት ወሳኝ ነው። በዛሬው ዕለት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን አሳትፎ የተካሄደው መድረክ በ5 ነጥብ 4 በመቶ እያደገ የመጣውን የከተሞች የሕዝብ ቁጥር ፍላጎት በጋራ ለመመለስ የሚያስችል አሰራር ለመዘርጋት እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም በተበታተነ አካሄድ የከተሞችን እድገት ለማሻሻል ሲተገበር የነበረው አሰራር የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ የተናገሩት ኢንጅነር አይሻ፤ ''በጋራ መስራት ግድ ነው'' ብለዋል። የትብብር አሰራሩ በሚኒስቴሩ የሚመራ ሲሆን የማህበረሰብ ተወካዮች፣ ለጋሽ ድርጅቶች፣ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች፣ የመንግስትና የጥናትና ምርምር ተቋማት በጋራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል። የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመቃኘት የጋራ እቅድ እንዲኖር በማድረግ በከተሞች በስፋት የሚስተዋለውን የስራ እድል ፈጠራና የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት የሚሰራኑንም ገልጸዋል። ከተሞች ውብ፣ ጽዱና አረንጓዴ እንዲሆኑ የአገሪቱ ልማትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቡ እንዲመታ ሁሉም እንዲተባባር ጥሪ አቅርበዋል። ከተመድ የከተማ ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ሃላፊ አቶ አክሊሉ ፍቅረስላሴ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የከተሞች እድገት ላይ የሚታየው ውስንነት አንዱ መንስኤ ተቋማት የጋራ አሰራር የሌላቸው በመሆኑ ነው። በተመድ ለቀጣዮቹ 20 ዓመታት ከተሞች እድገት ምን መምሰል እንዳለበት እቅድ መነደፉን ገልጸው፤ ዕቅዱን በኢትዮጵያ ለማስተግበር አዲሱ የከተሞች የትብብር አሰራር አጀንዳ ወሳኝ እንደሆነ አመልክተዋል። ''የተመድ የከተማ ኤጀንሲ በአገሪቱ የከተሞችን እድገት ለማፋጠን በሚሰራው ስራ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል'' ሲሉ አቶ አክሊሉ ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም