ቀጥታ፡

የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት የመጨረሻ ሶስት እጩዎች ታውቀዋል

ጥቅምት 19 ቀን 2012 (ኢዜአ)   የዘንድሮው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት በእግር ኳስና አትሌቲክስ የመጨረሻ ሶሶስት እጩዎች ተለይተዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ስራ ሃላፊዎች በሶስተኛው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት የሚበረከተው በ2011 ዓ.ም በእግር ኳስና አትሌቲክስ ውጤታማ ለሆኑ ስፖርተኞችና በኢትዮጵያ ስፖርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከተ/ች እውቅና ለመስጠት ነው። ስምንት የስፖርት ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በአባልነት ያቀፈው የቴክኒክ ኮሚቴ በእግር ኳስና አትሌቲክስ በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ አስር አስር ሰዎች በእጩነት አቅርበዋል። በዚሁ መሰረት ከመስከረም 14 ቀን 2012 ዓ.ም አድማጭና ተመልካቾች በ800 አጭር የጽሁፍ መልዕክት እስከ ትናንት በስቲያ 17 ሺህ 872 የስፖርቱ ቤተሰቦች ለስፖርተኞች ድምጽ ሰጥተዋል። የስፖርት ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች አጠቃላይ ለስፖርተኞቹ ከሚሰጠው ነጥብ 75 በመቶውን ሲይዙ 25 በመቶውን የስፖርት ቤተሰቦች ይዘዋል። በዚሁ መሰረት ዛሬ አጠቃላይ በተሰጠው ድምጽ መሰረት በእግር ኳስና አትሌቲክስ በሁለቱም ጾታዎች የመጨረሻ ሶስት እጩዎች ተለይተው ታውቀዋል። በዚሁ መሰረት በወንዶች እግር ኳስ የመቐለ ሰብዓ እንደርታው ተጨዋች አማኑኤል ገብረሚካኤል የፋሲል ከነማዎቹ ያሬድ ባየህና ሱራፌል ዳኛቸው የመጨረሻ ሶስት እጩዎች ውስጥ ተካተዋል። በሴቶች እግር ኳስ የአዳማ ከተማዎቹ ተጨዋቾች ሴናፍ ዋቁማና ሰናይት ቦጋለ እንዲሁም እመቤት አዲሱ (መከላከያ/ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) የመጨረሻ እጩዎች ውስጥ መካተት ችለዋል። በአትሌቲክስ ከወንዶች ሞስነት ገረመው፣ ጌትነት ዋለና ሰለሞን ባረጋ ሲመረጡ ከሴቶች አትሌት መቅደስ አበበ፣ ፋንቱ ወርቁና ለተሰንበት ግደይ የመጨረሻዎቹ እጩዎች ሆነዋል። የሽልማቱ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጋዜጠኛ ግርማ በቀለ ወቅታዊ ብቃት፣ውጤታማነትና ስፖርተዊ ጨዋነት በሁለቱም ጾታዎች በዋንኛነት የተቀመጡ መስፈርቶች ናቸው ብሏል። በእግር ኳስ የክለብ ውጤታማነት አብዛኛውን ድርሻ መያዙንና በአትሌቲክስ በአገር ውስጥ፣ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ያላቸውን ውጤታማነት በዋንኛነት ከግምት ውስጥ እንደገባ ገልጿል። ስፖርተኞቹን ለመለየት በ2011 ዓ.ም የነበራቸውን ብቃት ለመዳሰስ ጥረት እንደተደረገም ተናግሯል። ይሁን እንጂ ጥልቀት ያለው ግምገማ ተደርጓል ለማለት እንማይቻል ጠቅሷል። ለዚህም ውድድሮችን በቋሚነት የሚከታተል ቡድን አለመኖሩና መረጃዎችን የማደራጀት ክፍተት አንደነበረ እነዚህ ክፍተቶች በቀጣይ ሽልማቶች ላይ እንደሚስተካሉ ነው ጋዜጠኛ ግርማ የገለጸው። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የመዝናኛና ስፖርት ቻናል ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ቃሲም በበኩላቸው ተቋሙ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ሽልመቱን እየሰጠ ነው ብለዋል። በመጀመሪያ የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት በእግር ኳስና አትሌቲክስ በሁለቱም ጾታዎች ሽልማት መሰጠቱንና  በ2011 ዓ.ም የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ዘርፍ መካተቱን አስታውሰዋል። በአጠቃላይ በእግር ኳስና አትሌቲክስ የሽልማቱ አሸናፊዎች እያንዳንዱ 75 ሺህ ብር እንደሚሸለምና የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የ50 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚያገኝ ጠቁመዋል። በቀጣይ ተቋሙ የሚሸልመውን የገንዘብ መጠንና የሽልማት ዘርፎች እንደሚያሳድግ ገልጸው በሌሎች መስኮችም ሽልማት ለመስጠት እቅድም እንዳለውም አክለዋል። የአሸናፊዎች የሽልማት ስነ ስርአት ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም በቦሌ ስካይላይት ሆቴል እንደሚካሄድና ሽልማቱ በቴሌቪዥን፣በሬዲዮና በኦንላይን ስትሪሚንግ የቀጥታ ስርጭት እንደሚያገኝም ታውቋል። በሁለተኛው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት በእግር ኳስ በወንዶች አብዱልከሪም መሐመድ በሴትቶች ሰናይት ቦጋለ በአትሌቲክስ ደግሞ አትሌት ሰለሞን ባረጋ እና አትሌት ገንዘቤ ዲባባ አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል። አንጋፋው የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ የሕይወት ዘመን ተሻላሚ እንደነበሩም አይዘነጋም።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም