ቀጥታ፡

ፖሊስ ህዝቡን በእኩል የማገልገል ስብዕና ሊላበስ ይገባል....አቶ ርስቱ ይርዳው

ሀዋሳ ጥቅምት 19 / 2012  -- የክልሉ ፖሊስ ህዝቡን በዕኩልነት የማገልገል ስብዕና ሊላበስ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለፁ። በክልሉ ለሚገኙ መካከለኛና ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች ላለፉት ዘጠኝ ቀናት ሲሰጥ የቆየው ሁለተኛ ዙር ሥልጠና ተጠናቋል ፡፡ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በስልጠናው ማጠናቀቂያ መርሀግብር ላይ ተገኝተው ለሰልጣኞች የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል። የፖሊስ ኃይሉ ለአገራዊ ለውጡ ስኬታማነት የሚጠበቅበትን እገዛ እንዲደርግና የተሰጠውን የህዝብ ውግንና ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጣ ለማስቻል ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን አመልክተዋል። ህዝቡ በነጻነት ወጥቶ ሊገባ የሚችለው በሕግና በሕግ አስከባሪዎች መተማመን ሲችል መሆኑን የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ "ፖሊሳዊ ኃላፊነት ህብረተሰቡን በዕኩልነት ለማገልገል የሚሸከሙት ትልቅ አደራ ነው" ብለዋል ፡፡ ባለፉት ዓመታት የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች የፖሊስ ኃይሉ በህዝቡ ዘንድ ያለው አመኔታ እንዲሸረሸር አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ለእዚህም ተከስተው በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ጥቂት የፖሊስ አባላት ያልተገባ ተግባር መፈጸማቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ "ፖለቲካ ቢለዋወጥም የፖሊስ ኃይሉ ከህዝቡ ጋር የሚቀጥል በመሆኑ ጊዜያዊ በሆነ ማዕበል መዋጥ የለበትም" ብለዋል፡፡ የፖሊስ ኃይሉ በአመራሩ ፍላጎት ከመሳብ ይልቅ ሙያዊ ሥነ ምግባርን ተከትሎ ሕግን የማስከበር ሥራ ለሁሉም በፍትሀዊንት መስራት እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል፡፡ ባለፉት የተወሰኑ ዓመታት የፖሊስ ኃይል ተቀባይነቱን እንዲያጣ ያስገደዱና ክልሉን ዋጋ ያስከፈሉ ስህተቶች መፈፀማቸውን አቶ ርስቱ አስታውሰው፣ ፖሊስ ሁሉንም ህዝብ በዕኩልነት የማገልገል ስብዕና ሊላበስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ እንደአቶ ርስቱ ተገለጻ በአሁኑ ወቅት የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ ህዝቡ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምሯል። ለእዚህም የጸጥታ ኃይሉና የህብረተሰቡ ትብብር አስተዋጽኦ እንደነበረው ጠቁመው፣ "ይህንን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ የተለያዩ አካላት ጥረት ይጠይቃል" ብለዋል ፡፡ የደቡብ ክልል ብዝሀነትን የተጎናፀፈ፣ በርካታ የዳበሩ የሠላምና የአብሮነት እሴቶች ያሉበት በመሆኑ ህብረተሰቡን አስተባብሮ ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ ነው የገለጹት። ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በክልሉ የቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ አባል ኮማንደር አደመ ኃይሌ በስልጠናው ክልላዊና ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ግንዛቤ መያዛቸውን ጠቁመዋል። "ሥልጠናው የነበሩብንን ክፍተቶች በመሙላት ህዝቡን በሚፈለገው ልክ እንድናገለግል የሚያስችለንን አቅም ፈጥሮልናል" ብለዋል ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ፖሊስ ሙያዊ ሥነ ምግባሩን ጠብቆ ባለመስራቱ ከሕብረተሰቡ ጋር የሚነጥለው ሁኔታ መፈጠሩን አስታውሰዋል፡፡ በስልጠናው ያገኙት ግንዛቤ ተጠቅመው በቀጣይ ሕብረተሰቡን ለመካስ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። በአመራራቸው ሥር ያሉ የፖሊስ አባላት ለህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ሀገራዊ ለውጡን እንዲያሳኩ ጠንክረው እንደሚሰሩም ነው ኮማንደር አደመ የገለጹት ፡፡ የሲዳማ ዞን ፖሊስ ኢንስፔክተር መሠረት የኋላሸት በበኩላቸው ፖሊስ የህብረተሰቡን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስከበር የሚችለው ራሱ ለህግ ተገዥ ሲሆን መሆኑን ገልጸዋል፡፡"ከዚህ በኋላ የበደልነውን ህዝብ ለመካስ የሚያስችል ትክክለኛ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተናል" ብለዋል፡፡ ለዘጠኝ ቀናት በተሰጠው ስልጠና የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳና የከተማ አስተዳደር መካከለኛና ከፍተኛ የፖሊስ አመራር አካላት ተሳትፈዋል ፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም