ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ንግድን በቀላሉ ለመጀመር የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ፈጥና ልትተገብር ይገባል ተባለ

ኢዜአ ጥቅምት 19/2012 ኢትዮጵያ በቀላሉ ንግድን ለመጀመር የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን በፍጥነት ወደ ተግባር ማስገባት እንዳለባት ተገለጸ። ባለፈው ሳምንት የዓለም ባንክ ያወጣው ሪፖርትኢትዮጵያ በቀላሉ ንግድ መጀመር አስቸጋሪ ከሆነባቸው አገሮች ተርታ ተመድባለች። በሪፖርቱ አገሪቱ በዓለም በቀላሉ ንግድን መጀመር ከማይቻልባቸው 190 አገሮች 159ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ይህን ችግር ለመፍታትም  ካለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ጀምሮ ከ10 ተቋማት የተወጣጣ አገር አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሙ እየሰራ ይገኛል። ኮሚቴው በዋናነት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የገቢዎች ሚኒስቴር እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ነው። ይኸው ኮሚቴ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የተያዙ ዕቅዶች አፈጻጸም ላይ ዛሬ ውይይት አድርጓል። በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ ያገኘችው ደረጃ በ10 የተለያዩ ዘርፎች እንደ አገር ያለውን ውጤት መሰረት አድርጎ ነው ተብሏል። ከእነዚህ ዘርፎች መካከል በግንባታው ዘርፍ በተለይም በፈቃድ አሰጣጥና በንብረት ምዝገባ ላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡ ተገልጿል። የግንባታ ፈቃድ አሰጣጡ በ24 ደረጃ ከፍ ያለ ሲሆን የግንባታ ፈቃድ ባለሙያዎች አስፈላጊ የሙያ ብቃት እንዲኖራቸው አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍም ወጥቷል። አንድ ሰው ንብረት ገዝቶ በሚያስመዘግብበትና ንብረቱን ለሌላ ወገን በሚያዘዋውርበት ሂደት ላይ ያሉ አሰራሮች ግልጽ እንዲሆኑ መደረጉም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ማግኘቱ ነው የተነገረው። ይሁንና በአንድ ኩባንያ ውስጥ አነስተኛ ድርሻ ያላቸው ባለሃብቶች ያላቸው የህግ ከለላና ጥበቃ አነስተኛ መሆን አገሪቱ 18 ነጥቦችን እንድታጣ ማድረጉ ተገልጿል። በተለያዩ ተቋማት በአጭር ጊዜ የተከናወኑ ማሻሻያዎች ያሉ ቢሆንም በፍጥነት ወደ ተግባር ባለመግባታቸው ኢትዮጵያ ያላትን ደረጃ እንዳታሻሽል አድርጓል ነው የተባለው። የንግድ ህጉ ማሻሻያ፣ የኦንላይን የንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት፣ የኦንላይን ክፍያዎች በሁሉም ባንኮች መፈጸም፣መካከለኛ ግብር ከፋዮች ኦንላይን ግብራቸውን እንዲከፍሉ ማድረግ፣ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በማስያዝ ብድር ማግኘት ወደ ተግባር ካልገቡ ማሻሻያዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ በቀላሉ ንግድን ለመጀመር የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን በፍጥነት ወደ ተግባር ማስገባት አለባት ብሏል ኮሚቴው። የዓለም ባንክ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ሁለት ተጨማሪ የመገምገሚያ መስፈርቶችን የጨመረ ሲሆን እነርሱም በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ያለው ግንኙነት እና የመንግስት ግዥ ግልጽነት ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም