ቀጥታ፡

የውጭ ምንዛሬ ጭማሪ ማስተካከያ የወጪ ንግዱ እንዲነቃቃ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 12/2010 የብር የመግዛት አቅም ከዶላር አኳያ እንዲዳከም ከተደረገ በኋላ የወጪ ንግድ ገቢ መነቃቃት እያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ። ባንኩ በወጪ ንግድ ብቻ ሳይሆን የሃዋላ እና አገልግሎት ገቢ ላይም ለውጦች እየታዩ መሆኑ ተመልክቷል። ብሔራዊ ባንክ በጥቅምት 2010 ዓ.ም የብር የመግዛት አቅም ከዶላር አኳያ በ15 በመቶ እንዲዳከም ማድረጉ ይታወሳል። የዚህም ዋነኛ ዓላማ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የወጪ ንግድ ለማበረታታት ታሳቢ ተደርጓል። ይህም የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጪ የሚልኩ አምራቾችን ለማበረታታት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን ደግሞ ለመቀነስ ነው። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ኢኮኖሚ ትንተናና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተጠባባቂ ዳሬክተር አቶ ፍቃዱ ድጋፌ እንደሚሉት፤ እየተጠናቀቀ ካለው 2010 ዓ.ም በፊት ባሉት ተከታታይ ሶስት ዓመታት የወጪ ንግድ እየቀነሰ መጥቷል። እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ የብር የመግዛት አቅም ከዶላር አኳያ እንዲዳከም ከተደረገ በኋላ ባሉት ዘጠኝ ወራት ወደ ውጪ የሚላኩ እቃዎች ገቢ አወንታዊ ለውጥ አሳይቷል። ለውጥ ካሳዩ ምርቶች መካከልም ወደ ውጭ የተላከው የቡና መጠን 14 በመቶ ጭማሪ በማስመዝገቡ ከቡና ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በሁለት ነጥብ ሰባት በመቶ ለውጥ ማሳየቱን ነው ያብራሩት። በተመሳሳይ የቅባት እህሎችም በ24 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ያሳዩ ሲሆን፤ በአጠቃላይ የብር የመግዛት አቅም ከዶላር አኳያ መቀነሱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ የተገኘውን ገቢ በአራት ነጥብ ሦስት በመቶ ለውጥ ማሳየቱን ነው ያመለከቱት። ይህም ባለፉት ሶስት አመታት እየተቀዛቀዘ የመጣውን የውጪ ንግድ እንዲያንሰራራ እያደረገው መሆኑን ነው ያመለከቱት። ብር መዳከሙ የግል የሃዋላ ላይም አወንታዊ ተጽእኖ እያመጣ ሲሆን፤ በ26 ነጥብ 4 በመቶ እንዲያድግ ረድቷል። በቀጣዮቹ ወራትም ባለፉት ሶስት አመታት የነበረውን የወጪ ንግድ "ገቢ ይጨምራል" የሚል ትንበያ እንዳለ ነው ያነሱት።  የብር የመግዛት አቅም መዳከም የአገሪቷን ምርት በውጭ አገሮች ርካሽ ማድረግና ወደ አገር የሚገቡትን ማስወደድ መሆኑን የዘርፉ መላምቶች ያሳያሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባቀረቡት ሪፖርት ባለፉት ወራት የውጭ ንግዱ ገቢ  ለውጥ እያሳየ መምጣቱን አብራርተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም