የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ ከፍተኛ ምርት እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ ከፍተኛ ምርት እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ

አዲስ አበባ ጥቅምት 19/2012 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በመጀመራቸው ምርታማነታቸው መጨመሩን ይናገራሉ። የክልሉ ግብርና ቢሮ በበኩሉ ባለፈው የክረምት እርሻ ወቅት የተከናወነው ተግባር ምርታማነትን በማጠናከር ከፍተኛ ምርት ለመሰብሰብ የሚያስችል ሁኔታን ፈጥሯል ብሏል። በክልሉ በምርት ስብሰባ ወቅት የምርት ብክነት እንዳያጋጥም የተለያዩ የስራ ዕቅዶች እየተዘጋጁ መሆኑም ታውቋል። በክልሉ ግብርና ቢሮ የስራ ኃላፊዎች የተመራ ልኡክ በሰሜን ሸዋ ዞን ሶስት ወረዳዎች እየተከናወነ ያለውን የግብርና ስራ ጎብኝቷል። የልኡካን ቡድኑ በደገም ሂዳቡ አቦቴና ወራ ጃርሶ ወረዳዎች በኩታ ገጠም ዘዴ የተከናወኑ የእርሻ ሥራዎችን ጎብኝቷል። ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ተመሳሳይ የአየር ንብረት እና የመሬት አቀማመጥ ያላቸው የአርሶ አደር ማሳዎችን አንድ ላይ በማጣመር ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆነ ሰብል በስፋት ለማምረት የሚያስችል ስልት ነው። ይህም በአንድ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች ተመሳሳይ ሰብል በስፋት በማምረት ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ነው አርሶ አደሮቹ የሚናገሩት። በጉብኝቱ የተሻሻለ የገብስ፣ የጤፍና ማሽላ፣ ቅመማ ቅመም እንዲሁም የወተትና የእንቁላል ግብርና ሥራዎች ታይተዋል። በወራ ጃርሶ ወረዳ በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ የተሻሻለ የጤፍ ዝርያን በመጠቀም የተከናወነው የእርሻ ሥራ ምርታማነትን እያሳደገ መሆኑን አርሶአደር አየለ ለገሰ ይናገራሉ። ዘንድሮ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን ከመጠቀም ባሻገር ከሌላው ጊዜ በተሻለ ግብዓት በመቅረቡ በሄክታር እስክ 32 ኩንታል ምርት እንደሚሰበስቡ አርሶ አደሩ ገምተዋል። ይህም ሆኖ ከምርት መሰብሰብ ጋር በተያያዘ የምርት ብክነት እንዳያጋጥም ምርት የመሰብሰብ ተግባሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ይሆን ዘንድ መንግስት እገዛ እንዲያደርግ አርሶአደሩ ጠይቀዋል። በሂዳቱ አቦቴ ወረዳ በዚሁ በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ ማሽላ የዘሩት አርሶ አደር አራጌ ምትኩ "ቀድሞ ጠፍ የነበረ መሬት ወደ ምርታመነት ተቀይሯል" ነው የሚሉት። ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ከአንድ ሄክታር ከ5 ኩንታል የሚበልጥ የማሽላ ምርት አይገኝም ነበር፤ አሁን ግን ምርቱ በሶስት እጥፍ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋ። መንግስትም ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት የጀመረውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። በደገም ወረዳ በወተት ምርት የተሰማሩት አርሶ አደር መኮንን አራርሳ በቀን ከአንድ ላም በአማካይ ከ15 እስከ 25 ሊትር የወተት ምርት እያገኙ መሆኑን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በአካባቢው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለመኖሩ አርሶ አደሩ የልፋቱን ዋጋ እያገኘ አለመሆኑንም አስረድተዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ብርሐኑ በተያዘው ዓመት በዞኑ ከ12 ሚሊዬን ኩንታል በላይ የግብርና ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል። ይህ ይሳካ ዘንድ ምርጥ ዘርንና ማዳበሪያና ቴክኖሎጂን ጨምሮ የተለያዩ አስፈላጊ የግብርና ግብዓቶች እንዲሟሉ ተደርጓል ነው ያሉት። ዘንድሮ እንደ ጉድለት የታዩ ችግሮችን በመለየት በመጪው ዓመትም የግብርና ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግ እንሚሰራ ገልጸዋል። በዞኑ ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት ብክነት እንዳይኖር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ቅድም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ቢሮ ምክት ኃላፊ አቶ መብራቴ ገብረየሱስ በበኩላቸው እስካሁን ያለው ግምገማ የሚያሳየው ዘንድሮ በክልሉ ከፍተኛ የግብርና ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ይላሉ። በክልሉ በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ የተካሄደው የግብርና ሥራ እጅግ ውጤታማ በሆነ ይዞታ ላይ ይገኛል ሲሉም አክለዋል። ወደ ፊትም መንግስት ይህንኑ የአስተራረስ ዘዴ በማስፋት አርሶ አደሩን በግብርና ግብዓት ተደራሽ ለማድረግና በቴክኖሎጂ ለማገዝ እንደሚሰራ ገልጸዋል። እንድ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገላጻ ይህ የሚጠበቀው የተሻለ ምርት ብክነት እንዳያጋጠመው አርሶ አደሩ በቅርበት ይታገዛል ሲሉ አክለዋል።