ቀጥታ፡

በተከሰተው ሁከት የተሣታፉና ጉዳት ያደረሱ ሰዎች በሕግ ተጠያቂ መሆን አለባቸው - የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን

ጥቅምት 19/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) ሰሞኑን ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ተሣታፊ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጠየቀ።

ኮሚሽኑ ከጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀሰቀሰውን ግጭትና የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ከቀናት በፊት በተነሳው ሁከትና ግጭት ምክንያት ከ70 እስከ 80 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና በርካታ ንብረት መውደሙን  የመገናኛ ብዙሃን ዘገባን በመረጃነት በመጥቀስ ኮሚሽኑ በመግለጫው አመልክቷል።

ከእነዚህ ውስጥ አስር ያህሉ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት በጥይት ተመተው የሞቱ መሆናቸውን አክሏል።

ከዚህም ሌላ የሰዎች መደበኛ ኑሮ እና ሰላማዊ ሕይወት መረበሹን ያመለከተው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ በተጨማሪ የዚህ ዓይነቱ ተግባር የህግ የበላይነትን በእጅጉ የተፈታተነ መሆኑን ጠቁሟል።

በአገሪቷ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ አደጋ እና ስጋት  የጣለ እጅግ አሳሳቢ ክስተት መሆኑን አብራርቷል።

አብዛኛዎቹ ሰዎች በሁከቱ የተሳተፉ ሰዎች እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በግፍ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የተገደሉ መሆናቸውንም ኮሚሽኑ አሰታውቋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ "የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል"ያለው ኮሚሽኑ፤ በሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ የሚያወጡ የግለሰቦች፣ የሕዝብና የአገር ንብረት መውደሙን ጠቁሟል፡፡

እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ሆን ተብሎ በተፈጸመ ጥቃት ለጉዳት ተዳርገዋል ሲልም አክሏል፡፡

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ማናቸውም ዓይነት ቅሬታ ወይም ጥያቄ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ሊቀርብ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መኖሩን ኮሚሽኑ ጠቅሷል።

ለዚህ ውዝግብ መነሻ በሆነው ጉዳይ ላይ በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን ለመግለጽ የሚሹ ሰዎች እንደሚኖሩ ያመለከተው መግለጫው፤ ሁከት የቀሰቀሱ፣ የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ እንዲሁም ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ድጋፍ የሰጡ ሰዎች መኖራቸው ግን እንደማይካድ ኮሚሽኑ አክሏል።፡

ማናቸውንም ዓይነት ቅሬታና ጥያቄ በአመፅ እና በእልቂት ማስፈራሪያ ለማስፈፀም የታየው ተግባር እና የአስከተለው ጉዳት የሕግ የበላይነትን፣ የአገር ሰላም እና ሥርዓትን በአደባባይ በመገዳደር እና በመጣስ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ያስከተለ መሆኑንንም አስገንዝቧል።

በመሆኑም በየደረጃው በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በጥፋቱ ተሣታፊ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በሕግ ተጠያቂነታቸው መረጋገጥ አለበት ሲልም አሳስቧል፡፡

መግለጫው አክሎም "ይህን ጥፋት የፈፀሙ እና ወይም የጥፋቱን ተግባር እንደ መልካም ሥራ ያወደሱ ሰዎች ሁሉ በዱላ እና በስለት ተደብድበው በእሳት ተቃጥለው የተገደሉ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸውን ለአፍታ እንኳን በእራሣቸውና በቤተሰቦቻቸው ተክተው አለማሰባቸው የደረሰውን ጉዳት ይበልጥ መሪር አድርጐታል።

የድርጊቱ ተሳታፊዎች በደረሰው ጥፋት ማዘን መፀፀት እና ለሕግ የበላይነት መከበር የመተባበር ኃላፊነት እና ግዴታ አለባቸው" ብሏል።

መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አጥፊዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ ሳያወላውል እንደሚሠራ መግለጹ ተገቢ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ ይህ የመንግስት ኃላፊነት እና ተግባር በስልታዊ የምርመራ ሥራ እና በሕጋዊ ሥርዓት በአፋጣኝ በሥራ ላይ ሊውል እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

ከዚህ በመቀጠል ለሚደረገው የወንጀል ምርመራ ሥራ ማንኛውም ሰው በመተባበር እና ውጤቱን በትዕግስት በመጠባበቅ፣ በየአካባቢው የተጐዱ ሰዎችንና ቤተሰቦችን በማጽናናት በመደገፍ እና በመጠገን፤ እንዲሁም የመንግሥት፣ የፖለቲካ እና የልዩ ልዩ ቡድኖች መሪዎች የፖለቲካ ውጥረቱን ከሚያባብሱ ቆስቋሽ ንግግሮች እና ድርጊቶች እራሳቸውን እንዲቆጥቡ ያሳሰበው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እና ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ እንዲከበሩ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እና ይህን የመሰለ ጥፋት ዳግም እንዳይፈጸም የሚመለከታቸው አካሎች ሁሉ በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም